የሀገር ውስጥ ዜና

የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ተሳታፊዎች አዲስ አበባ እየገቡ ነው

By Melaku Gedif

July 08, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በሚካሄደዉ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ የሚሳተፉ ተወካዮች አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ከመጪው ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ይካሄዳል፡፡

በዛሬው ዕለትም በክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ በፌዴራል ደረጃ እንዲሁም በዳያስፖራው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ላይ ለመሳተፍ የተመረጡ ወኪሎች አዲስ አበባ መግባት ጀምረዋል፡፡

ተወካዮቹ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ÷  በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የምክክር ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ እድሉን በማግኘታቸው ከፍተኛ ሀገራዊ ስሜት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡

በምክክር ጉባዔው ላይ በሰከነ እና መደማመጥ በተሞላበት ስሜት የልዩነት ምንጭ የሆኑ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የምክክር ጉባዔው ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለዋናው ሀገራዊ ጉባዔ ስምንት ዐበይት አጀንዳዎችን ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።እነዚህም ፡-

👉 የሀገር ግንባታ

👉 የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት፣

👉 የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባና ድሬዳዋ ጉዳይ፣

👉  የሃይማኖት ጉዳዮች፣ታሪካዊ ቅሬታዎች እና እርቅ

👉 የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፣

👉 ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች

👉  ሙስና እና መልካም አስተዳደር እና የሰላም ግንባታ ናቸው፡፡

በአመለወርቅ መኳንንት