አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር ጦርነቱን ለማስቆም የተፈረመው ስምምነት አብቅቷል አሉ።
ፕሬዚዳንቱ የስምምነቱን መፍረስ የገለጹት በሁለቱ ወገኖች መካከል የተኩስ ልውውጥ ከተደረገ በኋላ ነው።
በቱርክ እየተካሄደ በሚገኘው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ስብሰባ ላይ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባደረጉት ንግግር የኢራን ተደራዳሪዎችን ተችተዋል።
የኢራን ተደራዳሪዎችን በወቀሱበት መልዕክታቸው መተማመን የማይቻልባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ አመልክተዋል።
የሁለቱ ወገኖች የጀመሩትን ድርድር መቀጠል እንደሚችሉ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ ይህ ግን ጊዜ ማባከን ካልሆነ በስተቀር ውጤት የማያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በሆርሙዝ ሰርጥ ላይ በነበሩ ሶስት የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ከ80 በላይ የኢራን ዒላማዎች ላይ ጥቃት መሰንዘሯን አሜሪካ ገልጻለች።
ለዚህ አጸፋ ደግሞ ኢራን በባህሬን እና ኩዌት በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ቢቢሲ ዘግቧል።
ኢራንን የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ የከሰሱት የኔቶ ኃላፊ ማርክ ሩቴ በበኩላቸው፤ አሜሪካ በኢራን ላይ የምትወስደው ርምጃ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤና የሀገሪቱ ተደራዳሪ ሞሃመድ ባገር አሜሪካ የተኩስ አቁም ስምምነቱን መጣሷን ተናግረዋል።
አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ለማድረግ እና በሁሉም ግንባሮች ያለውን ግጭት ለማስቆም የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ባለፈው ወር መፈረማቸው ይታወሳል።
በትዕግስት ግዛቸው