አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና ቦይንግ ኩባንያ የአቪየሽን ኢኖቬሽን ማዕከል በጋራ ለማቋቋም የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ የሚገኘውን የአቪዬሽን ዘርፍ ለማጠናከር እና በኤሮስፔስ ምህንድስና ትምህርት ውስጥ ፈጠራን ለማበረታታትና ብቁ የሰው ሃይል ለማፍራት ያለመ የተቋማቱ የረጅም ጊዜ የትብብር ማዕቀፍ ነው።
የቦይንግ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሔኖክ ተፈራ በወቅቱ እንዳሉት÷ በሚቀጥሉት ሁለት አስርት ዓመታት የአፍሪካ አየር መንገዶች ከ1 ሺህ 200 በላይ አዳዲስ አውሮፕላኖችን እና ከ74 ሺህ የሚበልጡ አዲስና ተጨማሪ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን ይፈልጋሉ፡፡
ስምምነቱ የኤሮስፔስ ኢንጂነሪንግ ተማሪዎችን አቅም ለማጎልበት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በተጨማሪም ቦይንግ አፍሪካ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው የከፍተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተማሪዎች ተሰጥኦቸውን የሚያዳብሩበት ስልጠናዎችን በጋራ ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ስምምነቱ ተቋማቱ በኤሮስፔስ ትምህርት፣ ምርምርና ፈጠራ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግር በጋራ እንዲሰሩ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በቀጣይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የስልጠና እና የምርመር ማዕከል ለመገንባት እንሠራለን ነው ያሉት፡፡
ማዕከሉ ከስልጠናዎች በተጨማሪ ለተማሪዎች እንደ 3ዲ ፕሪንተሮች፣ የበረራ ሲሙሌተሮች፣ የዲዛይን ሶፍትዌሮች የድሮን መገጣጠሚያ ኪቶችን ጨምሮ ዘመናዊ መሣሪያዎችን እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል፡፡
በደሳለኝ ቢራራ