አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እያጠናከረ ነው አለ የግብርና ሚኒስቴር።
የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ባለፉት ዓመታት በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የተገኙ ውጤቶችን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም የሌማት ትሩፋት ወተት፣ እንቁላል እና ዶሮ እርባታን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ምርታማነትን በማጠናከር ረገድ ተጨባጭ ውጤት አስገኝቷል ብለዋል፡፡
መርሐ ግብሩ በአራት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የምርት እድገት ማስመዝገቡን ገልጸው ÷ በቤተሰብ ደረጃ የእንስሳት ተዋጽኦ ምግቦችን የመጠቀም ሁኔታ እየተሻሻለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የምግብ ምርትን ከማሳደግ ባለፈ ለአርሶ አደሮችና ለከተማ ግብርና ተሳታፊዎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ በመፍጠር የቤተሰብ ኢኮኖሚን እያጠናከረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የሌማት ትሩፋት የወተት ምርት አቅርቦት ጅማሮውን በ7 ነጥብ 1 ቢሊየን ሊትር አድርጎ እንደነበር አስታውሰው÷ አሁን ላይ 15 ነጥብ 2 ቢሊየን ሊትር ወተት ወደ ማምረት ደረጃ መደረሱን አስረድተዋል፡፡
የዓሳ ምርት ተደራሽነትን በመላ ሀገሪቱ በማስፋት ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው 78 ሺህ ቶን ወደ 270 ሺህ ቶን እንዲሁም በዶሮ እርባታ 26 ሚሊየን የነበረው የጫጩት ሥርጭት ወደ 184 ሚሊየን ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በ2018 በጀት ዓመት 359 ሺህ ቶን የማር ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ 428 ሺህ ቶን መሰብሰብ መቻሉን አመልክተዋል።
የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን ማቅረብ፣ የእንስሳት ጤና አገልግሎትን ማጠናከር፣ የቴክኒክ ድጋፍና የግብዓት አቅርቦትን ማሻሻል ለተገኙት ውጤቶች ወሳኝ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።
በግዛቸው ግርማዬ