አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተኩስ አቁም ስምምነቱ አክትሟል ካሉ በኋላ አሜሪካ በኢራን ላይ ሁለተኛ ዙር ጥቃት ፈጸመች፡፡
ዋሽንግተን በዚህ ጥቃት ከ90 በላይ ኢላማዎችን እንደመታች የገለጸች ሲሆን፥ የኢራን ባለስልጣናት በበኩላቸው ይህ ጨዋታ አይደለም፤ ጥቃት ሲሰነዘርብን በዝምታ አንመለከትም በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡
አሜሪካ ባሳለፍነው ሰኞ በሆርሙዝ ሰርጥ በሚያልፉ ሦስት የንግድ መርከቦች ላይ ኢራን ጥቃት ፈፅማለች በማለት በወሰደችው የአጸፋ ርምጃ የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኃይልን 65 ወታደራዊ ጀልባዎች ማውደሟን ገልጻ ነበር፡፡
ቴህራን በምላሹ በአሜሪካ የቀረበባትን ውንጀላ ውድቅ በማድረግ በባህሬን፣ ኩዌት እና ኳታር በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት ፈፅማለች፡፡
የአሜሪካ ጦር ማዕእከላዊ ዕዝ (ሴንትኮም) ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተሰጠው ቀጥተኛ ትዕዛዝ መሰረት ከትናንት ምሽት ጀምሮ በፈጸመው ሁለተኛ ዙር ጥቃት 90 የሚሆኑ ወታደራዊ ኢላማዎችን መምታቱን አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ ጦር በሁለት ዙር በፈጸማቸው ጥቃቶች 14 ሰዎች መገደላቸውንና 78 ሰዎች መቁሰላቸውን የኢራን የጤና ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
ለቀናት ተግባራዊ ከተደረገው የተኩስ አቁም በኋላ ዳግም እየተካረረ የመጣውን የሁለቱ ሀገራት ጦርነት ተከትሎ የዓለም የነዳጅ ዋጋ በዚህ ሳምንት ብቻ 5 ከመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በእመቤት ሲሳይ