አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአእምሯዊ ንብረት ሥርዓት ለፈጠራና ዘላቂ ልማት ያለውን ሚና ለመጠቀም በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወልዱ ይመሰል፡፡
68ኛው የዓለም አእምሯዊ ንብረት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ ፈጠራን እና ዘላቂ ልማትን ለማበረታታት ያከናወነቻቸውን የሕግና የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አንስተዋል፡፡
አእምሯዊ ንብረት ለኢኮኖሚ ሽግግር፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለኢንዱስትሪ ልማት እንዲሁም ለፈጠራ፣ ለሀገር በቀል እውቀትና ለባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ስትራቴጂያዊ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአእምሯዊ ንብረት ማዕቀፏን በማዘመንና ቁልፍ በሆኑ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ በመሳተፍ ለአእምሯዊ ንብረት ሥርዓት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከብሪክስ አባል ሀገራት የአእምሯዊ ንብረት ተቋማት ኃላፊዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን፥ በቀጣይ በሕንድ በሚካሄደው የአባል ሀገራቱ ስብሰባ ላይ በሚቀርቡ አጀንዳ ዙሪያ ተስማምተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በብሪክስ አባል ሀገራት መካከል ያለውን የአእምሯዊ ንብረት ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗንም አንስተዋል፡፡