የሀገር ውስጥ ዜና

ዓለም አቀፉ የፓርላማ የመረጃና ደህንነት ፎረም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ

By Yonas Getnet

July 10, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዋና ትኩረቱን በፓርላማ አባላት፣ በመረጃ ባለሙያዎችና በመንግሥት ባለስልጣናት መካከል በዓለም አቀፍ የደህንነት ስጋቶች ዙሪያ ትብብር ለማጎልበት ያደረገ ዓለም አቀፉ የፓርላማ የመረጃና ደህንነት ፎረም መካሄድ ጀምሯል።

በፈረንጆቹ 2014 በአሜሪካ ኮንግረስ የቀድሞ አባል ሮበርት ፒቴንገር የተመሰረተው ፎረሙ፤ ዋና ተልዕኮው በሕግ አውጪው አካልና በአስፈፃሚው የመረጃና ደህንነት ተቋማት መካከል ያለውን ክፍተት ማጥበብ ነው።

በፎረሙ በፍጥነት እያደጉ የመጡ ድንበር ዘለል እና የቴክኖሎጂ ስጋቶችን ለመፍታት፣ የቀጣናውና የዓለም አቀፍ ሕግ አውጪዎችና የደህንነት ባለሙያዎች ይመክራሉ።

በዚህም ሕግና ቴክኖሎጂ የሚገናኙባቸውን የደህንነት ተግዳሮቶች መሠረት አድርጎ እንደሚመክር እና በዋናነት የሳይበር ደህንነት፣ ሕገወጥ ፋይናንስና ለሽብርተኝነት የሚውል የገንዘብ ምንጭን መከላከል እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን መከላከልን ጨምሮ ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል።

በፎረሙ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፓርላማ መረጃና ደህንነት ፎረም መስራቹ ሮበርት ፒቴንገር፣ የመንግስት ዋና ተጠሪ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቬን ማሲንጋን ጨምሮ ከ43 ሀገራት የተውጣጡ የፓርላማ አባላት እየተሳተፉ ነው።

ፎረሙ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት ይካሄዳል።

በዓለምሰገድ አሳዬ