ቢዝነስ

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ማዕቀፍ 15 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ያላቸው ሸቀጦችን ላከች

By Mikias Ayele

July 10, 2026

‎አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ማዕቀፍ በኩል ኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ምርቶቿን ወደ ውጭ መላክ ጀምራለች አለ።

ሚኒስቴሩ 9ኛ የባለድርሻ አካላት የሴክተር ጉባኤውን በሀዋሳ ከተማ እያካሄደ ነው።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በመድረኩ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በ2018 በጀት ዓመቱ ከወጪ ንግድ ዘርፍ 9 ነጥብ 4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት አቅዳ ከ11 ቢሊየን ዶላር በላይ አሳክታለች።

የተመዘገበው ገቢ ኢትዮጵያ ካላት እምቅ አቅም አንጻር የሚቀረው ቢሆንም ስኬቱ የመንግሥት የፖሊሲ ቁርጠኝነትና የቅንጅት ስራዎች ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ በአገልግሎት ዲጂታላይዜሽን፣ የንግድ ማህበረሰቡን የአገልግሎት እርካታ ማሳደግ እና የገበያ ማረጋጋት ላይ ስኬት መመዝገቡን ጨምረው ገልጸዋል።

የንግድ ሥርዓቱን ለማስከበር በተደረገ ክትትል ከ93 ሺህ በላይ በሚሆኑ ህገ ወጥ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ትስስር ረገድ ሀገሪቱ ትልቅ ስኬት ማስመዝገቧን ገልጸው፤ በተለይም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን የተከናወኑ ድርድሮች ውጤታማ በመሆናቸው በቀጣይ ዓመት የመጨረሻ ምላሽ የሚገኝ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህም የሀገሪቱን በዓለም መድረክ የመደራደር አቅም ከፍ የሚያደርግ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ማዕቀፍ ኢትዮጵያ ምርቶቿን ወደ ውጭ መላክ መጀመሯን ጠቅሰው፤ በቀጣናው ከተዘዋወረው 23 ሚሊየን ዶላር ውስጥ 15 ሚሊየን ዶላሩ ኢትዮጵያ በብቸኝነት የላከችው ነው ብለዋል።‎

‎በታሪኩ ለገሰ