አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል ውስጥ የተገነባውን አዲስ የላቀ የሕክምና ማዕከል መርቀው ሥራ አስጀምረዋል፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ ዛሬ ለታካሚዎች ዘመኑን የዋጀ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ “አዲስ የላቀ የሕክምና ማዕከል” መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ብለዋል።
ነባሩ ሆስፒታል በጣም በማርጀቱ ለታካሚዎች የማይመች መጨናነቅ ይስተዋልበት እንደነበር ጠቅሰው ÷ የነበሩት ኋላቀር የሕክምና መሳሪያዎች ለታካሚዎች ብቻ ሳይሆን ለባለሙያዎቹም አገልግሎት ለመስጠት ዘመኑን የዋጁ እንዳልሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
ይህንን አስከፊ ሁኔታ ታሪክ በማድረግ እጅግ ንፁህ ውብ የሆነ ባለ7 ወለል ሕንጻ ተገንብቶ ሥራ መጀመሩን ነው የገለጹት፡፡
ማዕከሉ በይዘቱ የሕክምና አገልግሎቶችን በእጅጉ የሚያሻሽል፣ የዘመኑ ቴክኖሎጂ የተሟላለት እና በነባሩ ሕንፃ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በእጥፍ የሚያሳድግ ነው።
የ2026 ምርቶች የሆኑና የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚጠቀሙ ዲጂታል ኤምአርአይ፣ ሲቲ ስካን፣ የአልትራ ሳውንድ፣ ተንቀሳቃሽ ኤክስሬይ፣ በሰዓት 30 ሺህ ሊትር የሚያመርት የኦክሲጅን ማምረቻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ቀድሞ የነበረውን የተኝቶ ሕክምና አልጋ ከ147 ወደ 360 ያሳደገ ሲሆን ÷ የኦፕሬሽን ክፍልን ከ3 ወደ 7 እንዲሁም የፅኑ ሕሙማን ሕክምና ክፍልን ወደ 19 አሳድጓል፡፡
አዲስ የላቀ የሕክምና ማዕከል ሰፊና የላቀ የድንገተኛ ሕክምና አገልገግሎት ደረጃውን ጠብቆ እንዲደራጅ መደረጉንም አመልክተዋል።
በተጨማሪም የሰራተኛ ማረፊያ ክፍሎች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ዘመናዊ ቢሮዎች፣ መሰብሰቢያ አዳራሾች እና የሰራተኛ ካፍቴሪያ አገልግሎት ለታካሚዎች በሚመች መልኩ ተገንብቶና ተደራጅቶ ለአገልግሎት በቅቷል ነው ያሉት።
ከንቲባ አዳነች የጤና አገልግሎት ፍላጎትን ለማሟላት የግሉን ዘርፍ በመደገፍ እና በማሳተፍ ወደ ውጭ በመሄድ ይደረግ የነበረውን ሕክምና በሀገር ውስጥ የሕክምና አገልግሎት መስጠት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ይህም ዓለም በዘርፉ የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ የተጀመሩ ሥራዎች ሕያው ምስክር እንደሆኑ ያመላከተ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
አዲሰ የላቀ የሕክምና ማዕከል በፍጥነትና በጥራት ተገንብቶ የላቀ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን የተወጡ አካላትንም አመስግነዋል።