የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል በድርቅ ተጠቂ የነበሩ አካባቢዎችን ወደ አምራችነት ያሸጋገረው የመስኖ ልማት…

By Melaku Gedif

July 10, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለመስኖ ልማት የተሰጠው ትኩረት በድርቅ ተጠቂ የነበሩ አካባቢዎችን ወደ አምራችነት አሸጋግሯል አለ የክልሉ ግብና ቢሮ፡፡

የቢሮው ም/ኃላፊ በሪሶ ፈይሳ እንዳሉት÷ በክልሉ የተዘረጉ ዘመናዊ አሠራሮች፣ የተሳለጠ የግብዓት አቅርቦት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር የግብርናውን ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በባህላዊ መሣሪያዎች ብቻ ተደግፎ የነበረው ግብርና ወደ ሜካናይዜሽን እየተሸጋገረ መሆኑ ትልቅ እምርታ ያመጣ ስትራቴጂካዊ ርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሜካናይዜሽን መስፋፋት አርሶ አደሩን ከዕለታዊ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ የሚሆን ምርት በስፋት እንዲያመርትና ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲሸጋገር በር ከፍቶለታል ነው ያሉት፡፡

በክልሉ በስፋት ተግባራዊ የተደረገው የኩታ ገጠም የእርሻ ሥርዓት፣ ይፋ የተደረጉትን የግብዓት አቅርቦቶችና የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን በአንድ ቋት በጥምረት ለመጠቀም ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል።

በክልሉ በስፋት የተተገበረው የኩታ ገጠም የስንዴ ልማት በበጋ መስኖ፣ በመኸር እና በበልግ ወቅቶች በተከናወኑ የተቀናጁ የልማት ሥራዎች ከ6 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ማልማት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህም ከ300 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ማምረት መቻሉን ጠቁመው÷ ውጤቱ የክልሉ ግብርና እየተመራበት ያለው አዲስ አቅጣጫ ውጤታማና ተስፋ ሰጪ ለመሆኑ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።

ቀደም ሲል በከፍተኛ ድርቅ ይታወቁ የነበሩ ቆላማ አካባቢዎችን ቀጣይነት ወዳለው አምራችነት ለመቀየር የተከናወኑ ተግባራት የዘርፉ ትልቅ ስኬቶች መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በተለይም በቦረና ዞን ወደ ሥራ የገቡት የፊና መስኖ ግድብና መሰል ፕሮጀክቶች የማኅበረሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በተግባር አረጋግጠዋል ነው ያሉት።

የመስኖ ፕሮጀክቶቹ አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ ለዘመናት ለውኃና ለሳር ፍለጋ ከቦታ ወደ ቦታ ያደርግ የነበረውን ጉዞና ባህላዊ የሕይወት ዘይቤ ከመሠረቱ መለወጣቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

እነዚህ ስትራቴጂካዊ ሥራዎች በአካባቢው ላይ የነበረውን እይታ በመቀየር ዛሬ ላይ ቆላማ አካባቢዎች ሰፊ የስንዴ ልማትና የመስኖ ማዕከል እንዲሆኑ ማስቻሉን አመልክተዋል፡፡