የሀገር ውስጥ ዜና

 ጠንካራ የባህር ኃይል ለብሔራዊ ጥቅም …

By Mikias Ayele

July 10, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በጂኦፖለቲካዊ አቀማመጧ እና በታሪካዊ የባሕር መዳረሻዎቿ የምትታወቅ ሀገር ብትሆንም፣ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ከባሕር በር መገለሏ ለብሔራዊ ጥቅሟ ትልቅ ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ የዘመኑን የዓለም የባሕር ላይ እንቅስቃሴዎች እና የኢኮኖሚ ደኅንነት በጥልቀት የተረዳው የለውጡ መንግሥት የኢትዮጵያ የባሕር ኃይልን እንደገና ወደ መድረክ እንዲመጣ አድርጎ የባህር ኃይሉ በውሃማ አካላት ላይ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የሚያስችል አስተማማኝ አቅም እየፈጠረ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር 1948 የተመሰረተ ሲሆን፤ በአፍሪካ የረጅም ጊዜ የምስረታ ታሪክ ካላቸው የባህር ኃይሎች መካከል አንዱ ነው፡፡

“የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የባህር ኃይል” የሚል ስያሜ የነበረው ይህ የባህር ኃይል ቋሚ የጦር ሠፈሩን በምፅዋ ወደብ ላይ በማቋቋም በ1950 ከንጉሠ ነገሥቱ የምድር ጦር እና የአየር ኃይል ጋር በመጣመር በኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ መምሪያ ሥር ሲተዳደር ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሮያል የባህር ኃይል ታሪክ እንደሚያስረዳው፤ ባህር ኃይሉ ሲቋቋም ጀምሮ ዋና ግዳጁ የነበረው በቀይ ባህር ጠረፎች ላይ ቁጥጥርና አሰሣ የማድረግ ቋሚ የቅኝት ግዳጅ ሲሆን ዋና ማዘዣው አዲስ አበባ እና ምፅዋ ላይ ነበር፡፡

የመከላከያ ሰራዊት መረጃ እንደሚያሳየው፤ በወቅቱ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር በኩል 1 ሺህ ኪሎ ሜትር የባህር በር የነበራት ሲሆን ከቀጣናው አልፋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ገናናቷን ያስመሰከረች ሀገርም ነበረች።

ይሁን እንጂ በ1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ መደረጉን ተከትሎ ኢትዮጵያ የባህር በሯን በሴራ ስታጣ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዕጣ ፈንታም መፍረስ ሆኗል።

ተቋሙ ለሶስት አስርት አመታት ገደማ የኢትዮጵያ መከላከያ አካል ሳይሆን ቆይቷል፡፡

ሆኖም ግን በቀይ ባህር እና በህንድ ውቅያኖስ የባህር ዳርቻ ያለውን የሀያላን ሀገራት ሽኩቻ እና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በጥልቀት የተረዳው የለውጡ መንግሥት በአዋጅ ቁጥር 1100/2011 የኢትዮጵያ ባህር ኃይል የመከላከያ ኃይሎች አካል ሆኖ ተቋቁሟል።

የባህር ኃይሉ የኢትዮጵያን የንግድ መርከቦች ደህንነት በማስጠበቅ በውሃማ አካላት ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ባሻገር በቀጣናው ያለውን የሽብርተኝነት ስጋት ለመቀልበስ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

የባህር ኃይል ዋና አዛዥ ሬር አድሚራል ክንዱ ገዙ እንደሚሉት÷ ተቋሙ የሠራዊቱን ወታደራዊ ዝግጁነት በማሳደግ እና ራሱን በማጠናከር ረገድ ስኬታማ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

በተለይም የኢትዮጵያ ባህር ኃይል የሰለጠነ የሰው ኃይል ልማት ሥራ፤ አቅም ግንባታ እና መሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን እና ለዘመናዊው የባህር ኃይል ግዳጅ አፈፃፀም ወሳኝ የሆኑ ባለሙያዎችንና መኮንኖችን እያፈራ ነው።

ለባህር ኃይሉ የሚያስፈልጉ የመሠረተ ልማት አውታሮችና ለተለያዩ የውሃ አካላት ግዳጅ የሚያስፈልጉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እና ቁሳቁሶች እየተሟሉ ሲሆን፤ ሰራዊቱ ከመርከቦች ደህንነት ጥበቃ በተጨማሪ በቀጣይ የባህር በር ደኅንነትን ለመጠበቅ የሚያስችለውን የውጊያ አቅምና ስትራቴጂካዊ ዝግጁነት በመገንባት ላይ ይገኛል።

ተቋሙ እየገነባ ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል እና ዘመናዊ የውጊያ አቅም፣ የንግድ መርከቦችን ከመጠበቅ ባለፈ በቀጣናዊ ሰላም እና ደኅንነት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ይፈጥራል።

ኢትዮጵያ በውሃማ አካላት ላይ ያላትን የሉዓላዊነትና የጋራ ተጠቃሚነት አላማ ለማሳካት፣ እየተከናወኑ ያሉት እነዚህ ስትራቴጂካዊ የአቅም ግንባታ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው የነገዋን ኢትዮጵያ የቀጣናዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ያረጋግጣል።

በሚኪያስ አየለ