አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል አንድ ኪሎ ዋት ሰዓት ኢነርጂ በ24 ብር ከ07 ሳንቲም ማቅረብ የሚያስችል አዲስ የኃይል አቅርቦት ስምምነት ተፈርሟል፡፡
የኃይል አቅርቦት ስምምነቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) እና የኬንያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጆሴፍ ሲሮር (ዶ/ር) ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኤሌክትሪክ ንግድ ለማጠናከር፣ በድንበር አካባቢዎች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማስፋፋትና የምስራቅ አፍሪካን የኢነርጂ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ያለመ ነው።
ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) በዚህ ወቅት ÷ የምስራቅ አፍሪካ ጎረቤት ሀገራት በአንድነትና በትብብር ሲሠሩ ትልቅና ስኬታማ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችሉ ይህ ስምምነት ማሳያ ነው ብለዋል።
ስምምነቱ ትስስሯ የተጠናከረ ምስራቅ አፍሪካን እውን ለማድረግ እንደሚያግዝ ጠቁመው ÷ ኢነርጂ የሀብት ምንጭ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሕዝብ ወደ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያደርስ ድልድይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ጆሴፍ ሲሮር (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ ስምምነቱ ከኃይል አቅርቦት ትስስር ባሻገር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ሰላምና የኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በተለይም በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር አካባቢ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ስምምነቱ ቀጥተኛ ተጠቃሚ መሆናቸው በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል።
ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የኃይል ትብብርና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከማሻሻል ባለፈ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተቀናጀ የኃይል አቅርቦት ሥርዓት ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት ትልቅ መነቃቃትን ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
በስምምነቱ መሰረት የኬንያው የኤሌክትሪክ ኃይል ኩባንያ በአንድ ኪሎ ዋት ሰዓት ኢነርጂ 24 ብር 07 ሳንቲም እንዲሁም ለዲማንድ ቻርጅ 1 ሺህ 10 ብር ከ89 ሳንቲም የሚከፍል ይሆናል፡፡
በመላኩ ገድፍ