የሀገር ውስጥ ዜና

በመደማመጥ፣ በመከባበር እንመካካር!

By Mikias Ayele

July 11, 2026

የሰው ልጅ በተፈጥሮው መደመጥን ይሻል። ሰው ሲደመጥ የሚፈጠርበት ደስታ በሀገር ደረጃ ደግሞ ትርጉሙ የላቀ ነው። የሚደማመጡ ዜጎች ሀገራቸውን እፎይ ያሰኛሉ። በአንጻሩ የመደማመጥ ባሕል ከተሸረሸረ ጭቅጭቅ ይነግሳል።

ሀገራዊ ምክክር ልብ ለልብ የመደማመጥ ተግባር ነው። የተለያዩ አመለካከቶች በአንድ ጠረጴዛ ላይ ቀርበው ሲመጋገቡ የጋራ መፍትሔን ያፈልቃሉ። ዜጎች ስለሀገራቸው ያላቸውን አመለካከት፣ ተስፋና ስጋት ያለገደብ ሲገልጹ የሀገር ባለቤትነት ስሜታቸው ይዳብራል።

በመደማመጥ መርሕ የሚከናወን ምክክር የአመለካከት ስብጥሩ ከፍተኛ ስለሚኾን ያለጥርጥር በማኅበረሰቡ ዘንድ ቅቡልነት ያለው መፍትሔን ያመነጫል። እርስ በእርስ ተደማምጠው የሚመካከሩ ዜጎች፤ ከመተዋወቅ የተሸመነ የአብሮነት ስሜትን ይቀዳጃሉ። የመደማመጥ የመጨረሻ ውጤቱ ደግሞ መከባበር ነው።

መከባበር ከጥልቅ መደማመጥ የሚፈጠር ሀገራዊ እሴት ነው። ለመከባበር በአመለካከት አንድ አይነት መኾን ግዴታ አይደለም።

አንዱ ኢትዮጵያዊ የሌላዋን ኢትዮጵያዊት የተለየ አመለካከት ሲያዳምጥ፤ እርሷም በተራዋ ስታደምጠው አንድ ላይ ተቀምጦ በመወያየት የሚፈጠር መከባበር በእያንዳንዳቸው ልቡና ውስጥ ቦታ ይይዛል። የተለየ አመለካከትን ለማዳመጥ ልብን መክፈት በተመካካሪዎች ዘንድ የአክብሮት መንፈስን ያሰፍናል።

ተደማምጠው የሚከባበሩ ዜጎች በጊዜ ሂደት መተማመንን እንደሚፈጥሩ እሙን ነው። መተማመን አንዱ የሌላዋን ሀሳብ ያምንበታል ማለት አይደለም።

ተደማምጦ በመከባበር ሂደት የአንድ ሀገር ልጅነት መቀራረብ ሲፈጠር፤ ጥርጣሬ ተሽሮ ወገናዊ የመተማመን እርሾ ይጠነሰሳል። እርስ በእርስ የሚተማመን ማኅበረሰብ ደግሞ ወደ ሀገራዊ መግባባት ይሸጋገራል።

ተደማምጠን እንመካከር፤ ተማምነን እንግባባ!

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን