የሀገር ውስጥ ዜና

ዓለም አቀፍ የደህንነት ፎረም ልዑካን አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኖሩ

By amele Demisew

July 11, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2018 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፍ የደህንነት ፎረም ልዑካን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግቢ በመገኘት አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡ በችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ የፓርላማ የመረጃ እና ደህንነት ፎረም መስራች እና ሊቀመንበር ሮበርት ፒተንገርን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የደህንነት ፎረም ልዑካን ቡድን አባላት ተሳትፈዋል፡፡ በተጨማሪም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ እና ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ ከተጋባዥ እንግዶቹ ጋር አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡ መርሐ ግብሩ የደህንነትና ፖሊሲ ጉዳዮችን ከመምከር ባሻገር ኢትዮጵያ በተግባር እያሳየች ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ተነሳሽነት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በቀጥታ የተካፈለበት አስደናቂ አጋጣሚ መሆኑን የም/ቤቱ መረጃ አመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያ እየተገበረችው በምትገኛው ግዙፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በ2018 የክረምት ወቅት ብቻ ከ8 ቢሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ሀገራዊ ግብ ተጥሎ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።