የሀገር ውስጥ ዜና

የቱርክዬ ኤኬ ፓርቲ ለብልጽግና ፓርቲ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈ

By Melaku Gedif

July 13, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቱርክዬ ገዢ ፓርቲ የሆነው የፍትህና ልማት ፓርቲ (ኤኬ ፓርቲ) ብልጽግና ፓርቲ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላስመዘገበው ስኬት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

የኤኬ ፓርቲ ም/ ሊቀመንበርና የፓርቲው የውጭ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ ዛፈር ሲራካያ ጉዳዩን አስመልክተው ለብልጽግና ፓርቲ ም/ ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ልከዋል፡፡

በመልዕክታቸውም በምርጫው የተገኘው ውጤት ወዳጅ ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም፣ ብልጽግናና ደህንነት በጎ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነትና ያላሰለሰ ጥረት ኢትዮጵያ ወደ መረጋጋት፣ ዘላቂ ልማትና ሁሉን አቀፍ ዕድገት የምታደርገውን ጉዞ አጠናክራ እንደምትቀጥል ሙሉ እምነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡

በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ለተመሰረተው መልካም ግንኙነትና ትብብር ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

በፈረንጆቹ መስከረም 30 ቀን 2025 የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት በፓርቲዎቹ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ ጠንካራ መሠረት መጣሉንም አውስተዋል፡፡

ለዚህም በብልጽግና ፓርቲ ወገን ለታየው ገንቢ አቀራረብ እና ምላሽ ከፍተኛ አድናቆት እንዳላቸው መግለጻቸውን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ በአዲስ መልክ ለብልጽግና ፓርቲ የሰጠው ውክልና በሁለቱ ፓርቲዎችም ሆነ በሀገራቱ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነትና ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ተጨማሪ ዕድሎችን እንደሚፈጥር በመልዕክታቸው ጠቁመዋል፡፡