አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተለያዩ ዘርፎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በዲጂታል አሰራር ለማዘመን የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት፡፡
አገልግሎቱ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በትብብር ያበለጸገውን ዲጂታል የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት መተግበሪያ በድሬዳዋ አስተዳደር በዛሬው ዕለት አስጀምሯል፡፡
ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ መተግበሪያው አገልግሎቶችን ከወረቀት ንክኪ ነጻ በማድረግ የዲጂታል ጉዞን ማፋጠን ላይ መሰረት ያደረገው ሪፎርም ሥራ አካል ነው፡፡
ለተለያየ አላማ የሚቀርብ ትክክለኛ መረጃ ለሀገር እድገት የሚቀረጹ ፖሊሲዎችን ለመተግበር ወሳኝ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ የበለጸገው ዲጂታል የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት መተግበሪያ የሕዝብን ጥያቄ በተቀላጠፈ የዲጂታል አሰራር መመለስ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ተቋማቸው የኢትዮጵያን የዲጂታል 2030 ጉዞ እውን ለማድረግ በተለያዩ ዘርፎች ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
መተግበሪውን ከድሬደዋ አስተዳደር የዲጂታል አገልግሎት ጋር በማስተሳሰር በትኩረት ይሰራል ያሉት ደግሞ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ሀርቢ ቡህ ናቸው፡፡
በአሸናፊ ሽብሩ