የሀገር ውስጥ ዜና

የሀገር በቀል ዕውቀት ለሀገራዊ ምክክር ስኬት…

By Melaku Gedif

July 13, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም ዙሪያ ሀገራት የፖለቲካ ቀውስ፣ የማኅበራዊ ክፍፍል እና የግጭት ሁኔታዎችን ለመሻገር አንዳንዶቹ በሕግና በፖለቲካ ማሻሻያዎች ላይ ሲያተኩሩ ሌሎች ደግሞ በብሔራዊ ምክክር አማካኝነት የጋራ መፍትሔ ለመፈለግ ሞክረዋል።

ሀገራት ዘላቂ ሰላም ለማጽናት በሚያደርጉት በዚህ ሒደት ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ብቻ ሙሉ በሙሉ መፍትሔ ማምጣት አይችሉም፡፡

በተለይም ሕዝቦች ለዘመናት ያዳበሩትን የሀገር በቀል ዕውቀትና ዕሴት በመጠቀም የሰዎችን ልቦና መፈወስና ማህበራዊ ትስስርን እንደገና መገንባት አስፈላጊ ነው፡፡

በማኅበረሰቦች ውስጥ ለብዙ ትውልዶች በተግባር የተፈተነ፣ በልምድ የተገነባና በባሕል የተወረሰ የአኗኗር ጥበብ የሆኑት እነዚህ የሀገር በቀል ዕውቀቶች ግጭትን በንግግር ለመፍታት፣ እርቅን ለማምጣት፣ ማኅበረሰብን ለማስታረቅና ከተፈጠረ ጉዳት በኋላ የጋራ ኑሮን እንደገና ለመገንባትን ያስችላሉ።

ሀገር በቀል ዕውቀትን በመጠቀም ችግሮችን በመፍታት ረገድ ልምድ ካላቸው ሀገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ አንዷ ናት፡፡ይህም ከአፓርታይድ ሥርዓት መውደቅ በኋላ ሀገሪቱ በበቀል ወይም በኃይል ሳይሆን በውይይትና በመግባባት ወደ አዲስ ምዕራፍ እንድትሻገር አስችሏታል።

ይህ “እኔ ስላለሁ አንተ አለህ፣ አንተ ስላለህ እኔ አለሁ” የሚለው የደቡብ አፍሪካ ጥንታዊ ዕሴት መደበኛ ብሔራዊ የውይይት መድረክ ባይሆንም፣ የዕርቁን፣ የጋራ መደማመጡን፣ የይቅርታን እና አብሮ የመኖርን መንፈስ የቀረጸ ባሕላዊና ሥነ ምግባራዊ ማዕቀፍ ሆኖ አገልግሏል።

በዚህም የእውነትና የዕርቅ ኮሚሽን በተቋቋመበት ወቅት የፍርድ ሒደቱ ሰዎችን በማግለልና በመቅጣት ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን የተበላሹ ግንኙነቶችን በመጠገንና ማህበራዊ ፈውስን በማምጣት ላይ እንዲያተኩር ያስቻለ ሀገር በቀል የሞራል ዕሴት ነው።

የሀገር በቀል ዕውቀት ዘመናዊ የመንግሥት ተቋማትን በእምነት፣ በመተማመንና በማኅበራዊ ቅቡልነት ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ የደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ አንድ ጠቃሚ ትምህርት ያስተምራል።

ኢትዮጵያም ያሏትን ለዘመናት የቆዩ በርካታ የሀገር በቀል የግጭት አፈታት ልምዶችን ከዘመናዊ የሕግና የፖለቲካ ተቋማት ጋር በማጣጣም ለሕዝብ ውይይት የሚያስፈልገውን እምነትና መተማመን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

እነዚህ ጥንታዊ ዕሴቶች ዘመናዊውን የመንግሥት አወቃቀርና የሕግ የበላይነት የሚያግዙ፣ ለሕዝብ ውይይቶች ጥልቀትንና መንፈሳዊ ጥንካሬን የሚሰጡ ተጨማሪ ሃብቶች ተደርገው ሊወሰዱ ይገባል።

በዚሁ መሠረት ኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅራኔዎቿን በዘላቂነት ለመፍታት ባለፉት ዓመታት ስታከናውን የቆየችውን የአጀንዳ ልየታ በስኬት በማጠናቀቅ፣ አሁን ላይ ታሪካዊና ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች።

ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ተወካዮች የሚሳተፉበት የሀገራዊ ምክክር ጉባዔም የዚህ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማሳያ ነው፡፡ ሒደቱ ሙሉ በሙሉ አካታችና ፍትሃዊ እንዲሆን የተለያዩ አመለካከት ያላቸውና ከተለያዩ የማሕበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ተወካዮች እየተሳተፉበት ይገኛል።

ይህ ታሪካዊ የምክክር እንቅስቃሴ የዜጎችን እምነትና ተሳትፎ በማሳደግ፣ ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት ትልቅ ዕድል የያዘ ሲሆን÷ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ከዘመናዊ የመንግሥት አወቃቀር ጋር በማጣመር የተባበረች ሀገርን ለቀጣዩ ትውልድ ለመስጠት ያስችላል።

ስለሆነም ለዚህ ታላቅ ሀገራዊ ግብ ስኬት እያንዳንዱ ዜጋ፣ የፖለቲካ ፓርቲና ባለድርሻ አካል የበኩሉን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባል።

በዮናስ ጌትነት