የሀገር ውስጥ ዜና

የኒውክሌር ኃይል ለኢትዮጵያ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት…

By Yonas Getnet

July 13, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኒውክሌር ኃይል የኢትዮጵያን ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ መሠረት ነው አሉ የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኢንጂነር አብዱራዛቅ ዑመር።

የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኢነርጂ ኮሚሽን ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ እና ከአፍሪካ የኒውክሊየር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር በመተባበር ከ17 ሀገራት በዘርፉ ለተውጣጡ ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ነው።

በመድረኩ ላይ ኢንጂነር አብዱራዛቅ ዑመር እንዳሉት፤ የኒውክሌር ኢነርጂ ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው።

ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማረጋገጥ የምታደርገው ጥረት ዘላቂነት ያለው የማይቆራረጥ ኃይል ይፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም ዕውቀትን መሰረት ያደረገ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።

አስተማማኝና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ዘላቂ የኃይል አቅርቦት ያስፈልጋል በማለት ገልጸው፤ በዚህ ረገድ የኒውክሌር ኃይል ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

የኒውክሌር ኃይልን ለሰላማዊ ዓላማ ለመጠቀም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን ለ11 ቀናት የሚቆይ ስልጠና እንድታዘጋጅ የተመረጠችው ከ17 ሀገራት ጋር ተወዳድራ በኒውክሌር ኃይል ልማት ያሳየችው ጅማሬ ተገምግሞ ተገልጿል፡፡

በዙፋን ካሳሁን