አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የደን ሽፋን ከነበረበት 14 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 18 ነጥብ 9 በመቶ ማሳደግ ተችሏል አሉ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ደረጀ ማንደፍሮ።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የዘንድሮው ክረምት የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደጀን ወረዳ ተካሂዷል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ደረጀ ማንደፍሮ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በክልሉ ባለፉት 7 ዓመታት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሔክታር በላይ መሬት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በተለያዩ ችግኞች ተሸፍኗል።
በዚህ ወቅት 10 ነጥብ 6 ቢሊየን በላይ ችግኞች መተከላቸውን እና የክልሉ የደን ሽፋን ከነበረበት 14 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 18 ነጥብ 9 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
በዘንድሮው የክረምት መርሐ ግብር አርሶ አደሩን፣ ወጣቶችንና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የችግኝ ተከላውን ስኬታማ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባሻገር የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ እንደሚገኝም ኃላፊው አስረድተዋል፡፡