የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ አበባ የ2019 በጀት 502 ነጥብ 27 ቢሊየን ብር ሆኖ ጸደቀ

By Yonas Getnet

July 13, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ባካሄደው 3ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባዔ በሁለተኛ ቀን ውሎው የአዲስ አበባ ከተማ የ2019 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ ተወያይቷል፡፡

በዚህም ም/ቤቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2019 በጀት ዓመት አጠቃላይ በጀት 502 ነጥብ 27 ቢሊየን ብር እንዲሆን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

የፀደቀው በጀት ከባለፈው የ2018 ዓ.ም ተመሳሳይ በጀት ጋር ሲነጻፀር የ152 ነጥብ 26 ቢሊየን ብር ወይም 43 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተመላክቷል፡፡

ከፀደቀው በጀት ውስጥ 359 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለካፒታል፣ 142 ነጥብ 97 ቢሊየን ብር ለመደበኛ ወጪ እንዲሁም 16 ቢሊየን ብር የመጠባበቂያ በጀት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በጀቱ የከተማ አስተዳደሩን የ10 እና የ5 ዓመት የልማት ስትራቴጂዎች ግቦችንና እና የትኩረት አቅጣጫዎችን ለማሳካት ያለመ መሆኑን የከተማዋ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢኮኖሚ ማረጋጋትና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል፣ የስራ እድል፣ ፈጠራ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ማጠናከር፣ የመሠረተ ልማት ግንባታና ጥገና በዘላቂነት ማረጋገጥ፣ የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችንና ኮሪደር ልማትን ለመጠበቅና ለማስቀጠል እንደሚውልም ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም የትራንስፖርትና የትራፊክ ፍሰትን ማሻሻል፣ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ብልሹ አሰራርንና ሌብነትን ማስቀረት፣ የሰው ሃብት ልማት የማስፈፀም አቅምን መገንባት፣ ሰላምና ፀጥታ ማረጋገጥ፣ የቤት ልማት ማጠናከር፣ የውሃ አቅርቦት እና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች በተሟላ ሁኔታ ለማጠናቀቅና የመንገድ መሰረተ ልማት ለማስፋፋት የሚውል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡