አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለመቄዶንያ የሚደረገው ድጋፍ ሰብዓዊነትን እና ለሕዝብ ዘብ መቆምን የሚያሳይ ተግባር ነው አሉ የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር መስራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠ፡፡
ሐምሌ 4 ቀንን ለመቄዶንያ የጉብኝትና የድጋፍ ቀን አድርጎ በመሰየም ላለፉት 3 ዓመታት ድጋፍና እገዛ ሲያደርግ የቆየው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በዚህ ዓመት የ2 ሚሊየን ብርና የአምቡላንስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉን አስመልክቶ ለፋና ዲጂታል ሃሳባቸውን የሰጡት ቢኒያም በለጠ እንዳሉት ÷ የተደረገው ድጋፍ አፋጣኝ የሕክምና እርዳታ ለመስጠት፣ ሕይወትን ለማትረፍና የከፋ ጉዳትን ለመከላከል የላቀ አስተዋጽኦ አለው፡፡
የተቋማቱ አብሮነት ለድርጅቱ ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬን ከመስጠት ባለፈ ችግሮችን በጋራ የመፍታት፣ ማህበራዊ ሰላምን የማጠናከርና ሰብዓዊነትን በተግባር የማሳያ መንገድ ነው ሲሉ አውስተዋል፡፡
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ያደረገው ድጋፍ ተቋሙ ለሀገርና ለሕዝብ ዘብ መቆሙን ያረጋገጠበትና ለሌሎች ተቋማትም ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
ሌሎች ታላላቅ ተቋማትም ከዚህ በጎ ተግባር ትምህርት በመውሰድ በቀጣይ ለድርጅቱ የሚያደርጉትን እገዛና ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለማህበሩ ከዚህ በፊት ለተደረገውና በቀጣይ ለሚደረገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በመቄዶንያ አባቶች እና እናቶች ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የርክክብ ሥነ ሥርዓቱ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት መካሄዱ ይታወሳል፡፡