የሀገር ውስጥ ዜና

ሰራዊቱ ሀገሩን በብቃት ከመጠበቅ ጎን ለጎን ችግኝ የመትከል የቆየ ባህል አለው – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

By Mikias Ayele

July 14, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሀገሩን በብቃት ከመጠበቅ ጎን ለጎን ችግኞችን የመትከል የቆየ ባህል አለው አሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፡፡

የዘንድሮው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በመከላከያ ጠቅላይ መመሪያ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል፡፡

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) እንዲሁም ከፍተኛ መኮንኖችና የተለያዩ ሀገራት አታሼዎች በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል፡፡

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚሁ ወቅት ሰራዊቱ ሀገሩን በብቃት ከመጠበቅ ጎን ለጎን ችግኞችን የመትከል የቆየ ባህል እንዳለው አስታውሰው፥ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የሰራዊቱን ችግኝ የመትከል ባህል ይበልጥ እንዳጠናከረው ገልጸዋል።

መርሐ ግብሩ የኢትዮጵያን የደን ሽፋን በመጨምር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን በመከላከል ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን በመግለጽ፥ ሰራዊቱ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

በዘንድሮው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 20 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉ ተመላክቷል፡፡

በሳራ ስዩም