የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ ምዕራፍ ታሪካዊ ጉዞ …

By sosina alemayehu

July 14, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ክፍተቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በታሪኳ ትልቅ የሆነውን የሀገራዊ ምክክር ሂደት እያከናወነች ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች አጀንዳዎችን ሲያሰባስብ የቆየ ሲሆን፤ አሁን ሕዝቡ በነጻነት እንዲወያይና በጋራ እጣ ፈንታው ላይ እንዲወስን እያደረገ ይገኛል።

ትልቅ ምዕራፍ ላይ የደረሰው ይህ ጉዞ ከነገ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈ ታሪካዊ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ያካሂዳል።

በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለሚቀጥሉት ሦስት ሳምንታት የሚቆይ ይሆናል፡፡

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ለመሳተፍ ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች፣ ከፌዴራል ተቋማት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ የተወጣጡ ከ4 ሺህ በላይ ተመካካሪዎች ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመግባት ላይ ይገኛሉ።

ኮሚሽኑ ለጉባኤው ተሳታፊዎች በሙሉ ስለ ውይይቱ ሥነ ምግባር፣ ሥርዓት እና የአሰራር ደንብ የቅድመ ምክክር ግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻ አድርጓል፡፡

የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ዋነኛ ግብ አሸናፊና ተሸናፊ የሚገኝበትን የቆየ የፖለቲካ ባህል በመቀየር፤ ሁሉም በጋራ የሚያሸንፍበትን ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ያለመ ነው።

ተመካካሪዎች በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብቶች እና የሀገር ግንባታ ዙሪያ ጨምሮ የቀረቡትን ዋና ዋና የአጀንዳ ምሰሶዎች በጥንቃቄ በመመርመር የጋራ መፍትሔዎችን ያስቀምጣሉ።

ነገ የሚጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያ ካለችበት ውስብስብ ችግር ወጥታ ወደ ተሻለ አንድነትና ማሕበራዊ መተማመን የምትሻገርበት ወሳኝ የታሪክ ድልድይ ነው።

የምክክር ጉባኤው የመላው ኢትዮጵያውያን የወደፊት የጋራ እጣ ፈንታ የሚወሰንበት በመሆኑ፤ የሁሉንም ወገን በሰከነ መንፈስ መወያየትና ርብርብ ይጠይቃል።

በሶስና አለማየሁ