የሀገር ውስጥ ዜና

የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ለጎብኚዎች ክፍት ሆነ

By Hailemaryam Tegegn

July 14, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የተገነባው ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ለጎብኚዎች ክፍት ሆኗል፡፡

በደቡብ ወሎ ዞን ከደሴ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተገነባው ሪዞርቱ ለጎብኚዎች ክፍት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ሪዞርቱ የወሎን አስደናቂ ተፈጥሯዊ ውበት ከዘመናዊ መስተንግዶ ጋር ያቀናጀ ሲሆን፥ በ13 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ አርፏል፡፡

ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ መልኩ የተገነባው ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ምግብ ቤቶች፣ መኝታ ክፍሎችን፣ የመዋኛ ገንዳዎችንና ሳቢ አረንጓዴ ስፍራዎችን በውስጡ አካትቷል፡፡

በተጨማሪም የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገዶች፣ የሄሊኮፕተር ማረፊያ እንዲሁም በተለያዩ የፍራፍሬ ዞኖችና በደን የተከበበ በመሆኑ ለቱሪስቶች ልዩ ትውስታን እንደሚፈጥር ነው የተገለጸው፡፡

ሪዞርቱ የወሎን ሕዝብ ባህላዊና ተፈጥሯዊ እሴቶች ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ የላቀ ሚና እንደሚጫወት ታምኖበታል።

በከድር መሀመድ