አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የጀመረችው የምክክር ጉባኤ ስኬት መላውን የአፍሪካ ቀንድ ወደ ብሩህ ተስፋ የሚመራ እርምጃ ነው አሉ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ዋና ፀሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት በይፋ መካሄድ ጀምሯል።
ዋና ፀሀፊው በወቅቱ እንዳሉት፥ የዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ረዥም እና አኩሪ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል።
በዓለም ላይ በግጭት የተገነባም ሆነ ያተረፈ ሀገር አለመኖሩን ጠቅሰው፤ ዛሬ የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሱ ሀገራት ቅድሚያ ለሰላምና ለውይይት በመስጠታቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድና በውይይት መፈታት እንደሚችሉ ገልጸው፤ ኢትዮጵያም የራሷን ቁስል የምታክምበትና ችግሮቿን የምትፈታበት የዕርቅ ሥርዓት ያላት ጥንታዊ ሀገር ናት ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን መልስ ፍለጋ ወደ ውጭ ከመመልከት ይልቅ የሀገር በቀል የሽምግልና እና የዕርቅ ዕሴቶቻቸውን በመጠቀም ወደ ውስጥ መመልከት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
ይህ አካሄድ የሀገሪቱን ውስጣዊ ችግሮች ከመፍታት ባለፈ ለአፍሪካና ለመላው ዓለም ጭምር ምሳሌ የሚሆን መፍትሔ ማምጣት እንደሚያስችል አመልክተዋል፡፡
የዛሬው ዕለት በፖለቲካ ባሕል ውስጥ መሠረታዊ የለውጥ ነጥብ መሆን እንዳለበትና ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ሙሉ በሙሉ ውድቅ ሊደረጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ኢትዮጵያውያን በውይይትና በመከባበር ልዩነቶቻቸውን መፍታት እንደሚችሉ ለዓለም አቀፉ ማሕበረሰብና ለራሳቸው የሚያስመሰክሩበት መድረክ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በጉባኤው ላይ የተሳተፉ አካላት ሁሉ የሚወክሉትን ሕዝብ፣ በተለይም በታላቅ ተስፋ የሚጠባበቁ እናቶችን፣ አባቶችንና ሕጻናትን በኃላፊነት ማሰብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ቀንዲልና ተምሳሌት እንደመሆኗ መጠን በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ግጭትና ስቃይ ሙሉ በሙሉ ሊያበቃ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢጋድ በዚህ ታሪካዊ የሰላም ጉዞ ውስጥ ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል፡፡
በዮናስ ጌትነት