የሀገር ውስጥ ዜና

የምክክር መድረኮች ስህተትን ለማረምና ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለመወሰን ዕድል ይሰጣሉ – ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ

By sosina alemayehu

July 15, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፖለቲካ የምክክር መድረኮች ስህተትን ለማረምና ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለመወሰን ዕድል ይሰጣሉ አሉ የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት በይፋ መካሄድ ጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፤ ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ተመሳሳይ ታሪክ አላቸው ብለዋል።

ሁለቱም ሀገራት የእርስ በርስ ጦርነት አጋጥሟቸው ነበር በማለት ገልጸው፤ የእርስ በርስ ጦርነት አውዳሚ ከመሆኑ ባሻገር አሸናፊ እና ተሸናፊ እንደሌለው አስገንዝበዋል።

በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት አጋጥሞን ከነበረው ምስቅልቅል መውጣት የቻልነው በምክክር ነው ያሉት ኦባሳንጆ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየሰራቸው ያሉ ስራዎችን በመጎብኘት አስደሳች ነገሮችን ተመልክቻለሁ ብለዋል።

የፖለቲካ ምክክር መድረኮች ስህተትን ለማረምና ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለመወሰን እድል ይሰጣሉ ነው ያሉት።

የአፍሪካ መዲና የሆነችው ኢትዮጵያ የተለያየ ማንነት ያለው ህዝቧ ትልቅ እድሏ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሶስት ዓመታት በፊት ሀገራቸው በስንዴ ምርት እራሷን ትችላለች በማለት የተናገሩት ሀሳብ የገባን በአሜሪካና ኢራን ጦርነት ስንፈተን ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለሌሎችም መትረፏን ጠቅሰው፤ ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንኳን ደስ ያለዎት፤ ያሰቡትን አሳክተውታል ማለት አፈልጋለሁ ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያዊነት ዓላማ ኢትዮጵያን ትልቅ ማድረግ መሆኑን በመጥቀስ፤ ይህንን ለማሳካት ሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አጽንኦት ሰጥተዋል።

በምሕረት ደምሴ