አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሀገራዊ ምክክር ጉባዔውን በኃላፊነት ስሜት የምናካሂድ ከሆነ ለልጆቻችን የበለጸገች እና የጸናች ኢትዮጵያን ማስረከብ እንችላለን አሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ÷ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ኢትዮጵያ በገዛ እጇ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የሚያስችላትን ብዕርና ብራና ያገኘችበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን የውይይትና ማህበራዊ ትስስር ባህል ከዋርካ ጋር በማስተሳሰር፤ ዋርካን ለሽምግልና፣ ለመማማር እና ለማረፍ እንጠቀምበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ግን ዋርካን የመቁረጥ ባሕል እየሰፋ መምጣቱን ጠቅሰው ÷ ከዚህ ጋር ተያይዞ የመተሳሰብ ባሕል እየጠፋ፤ እኔ የምፈልገው ብቻ ካልሆነ ወደሚል አደገኛ ባሕል እየተቀየረ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡
ውስጣችን ሰላም እንዲሆንና መልካም እንቅልፍ እንድንተኛ ለሰፈርና ወገን በማድላት ሳይሆን ሀገርን ታሳቢ አድርጎ መመካከር ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡‘’ለዛሬ አትምከሩ ፣ ለነገ ምከሩ፤ ለእናንተ አትምከሩ፣ ለልጆቻችሁ ምከሩ’’ ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ የትናንት ችግራችንን ፈትተን ለነገ መልካም መሰረት የምናኖርበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ እያንዳንዱ ተወካይ ሲወያይ ልጆቹን እያሰበ መሆን እንደሚገባው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
አንድ ቦታ በመቆም ብቻ በሌላ ወገን ያለውን ችግር መረዳትና ችግርን መፍታት እንደማይቻል ጠቅሰው ÷ ኢትዮጵያን ማጽናት የምንችለው እርስ በርሳችን መደማመጥ ከቻልን ብቻ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በቁጥር ትልቅ የሆኑ ሕዝቦች ትንሾችን በማክበር የእኛ ፍላጎትት ብቻ ይሁን ከሚል መንፈስ በመውጣት ለውይይቱ መሳካት የበኩላቸውን መወጣት እንደጠበቅባቸው አመልክተዋል፡፡
ማንንም በማይጎዳ መልኩ በጋራ መጠቀም የሚቻልባቸውን ሀገራዊ ጉዳዮች በማንሳትና ከሰፈር ሀሳብ በመውጣት ለኢትዮጵያ ማለት ሲቻል ምክክሩ ውጤታማ እንደሚሆን አብራትተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በምክክር ጉባዔው መተሳሰብን መሰረት በማድረግ ለኢትዮጵያ የሚበጃት ውጤት እንዲመጣ አደራ ብለዋል፡፡
በቤተልሔም ግርማ