የሀገር ውስጥ ዜና

ምክክሩ የፀና ቃልኪዳን የሚፈጠርበት ነው – ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር )

By abel neway

July 15, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በሀገሪቱ ታሪክ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በህዝብና በመንግሥት መካከል አዲስና የጸና የታመነ ቃልኪዳን የሚፈጠርበት ምዕራፍ ነው አሉ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)።

ኮሚሽነሩ ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉትን ቆይታ፤ ምክክር እንደ ህይወት ነው፤ ህይወት እስካለ ድረስ ሂደቱ ይቀጥላል ብለዋል። ምክክሩ ዘላቂ የሰላም ባህል ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፤ የሂደቱን ፍፁም አካታች ለማድረግ ኮሚሽኑ በሩ ክፍት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ልዩነቶችና ችግሮች ሲፈጠሩ ወደ ጫካ ሳይሆን ወደ ጠረጴዛ መምጣት ባህል እንዲሆን ማድረግ የሂደቱ ዋነኛ ስኬት መሆኑን ነው ያብራሩት።

ዛሬ ለተጀመረው የምክክር ጉባኤ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ 180 ቃለ ጉባኤ ያዦች የህዝቡን ድምፅ በገለልተኝነትና በሙያዊ ብቃት ይመዘግባሉ ብለዋል።

የምክክር ሂደት በይፋዊው መድረክ ማጠቃለያ የሚቆም ሳይሆን፣ ዜጎች በችግሮቻቸው ላይ በነፃነት መክረው ዘላቂ መፍትሄ የሚፈጥሩበት ቀጣይነት ያለው መንገድ መሆኑንም አመላክተዋል።

ኮሚሽኑ ያዘጋጃቸው የውሳኔ ሃሳቦች ህዝባዊ ተቀባይነትንና ተቋማዊ ድጋፍን አግኝተው ተግባራዊ እንዲደረጉ ይሰራል ነው ያሉት።

ይህ ታሪካዊ መድረክ ኢትዮጵያዊያን በጠረጴዛ ዙሪያ የመነጋገርን ባህል በማሳደግ የጋራ ነጋቸውን በራሳቸው እንዲቀርጹ አዲስ ተስፋ ሰጥቷል ብለዋል።

በቅድስት ዘውዱ

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ከፋና ፖድካስት ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለመከታተል ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ https://youtube.com/watch?v=QNonsr0i6nU&si=TAMQrxN4prAAP1OU