የሀገር ውስጥ ዜና

ሀገራዊ ምክክሩ የተቋጠረውን የምንፈታበት ጥበብ ነው

By Hailemaryam Tegegn

July 16, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር እንደ ቀላል አትገነባም፤ መከባበር፣ በኃላፊነት መነጋገር፣ በትዕግስት መደማመጥን ትሻለች ።

ጊዜውን በሚመጥን መልኩ እኛ ካለንበት አቅጣጫ ተዟዙረን ለማየትና ሌሎች እንዴት ያስባሉ የሚለውን ለመረዳት፣ ያላግባቡንን ጉዳዮች ለመፍታትና የታሪክ ስብራቶቻችንን ለመጠገን በመመካከራችን ብዙ እናተርፋለን፡፡

ይህ ምክክር ሀገራችን እንድትተራመስና ዜጎቿ በሀገር ጉዳይ አንድ መሆን እስኪያቅታቸው ድረስ እንደ ስጋት እንዲተያዩ በማድረግ ወደሚገባቸው አንድነትና ከፍታ እንዳይራመዱ ሰቅዘው የያዙ ውስብስብ ቋጠሮዎች የሚፈቱበት ታሪካዊ እድል ነው፡፡

ሀገራችንን አናስደፍርም ያሉ አባቶቻችን ከጠላት ጋር ተጋፍጥጠው በዱር በገደሉ ተዋድቀውና ዋጋ ከፍለው ሉዓላዊት ኢትዮጵያን ለዛሬ አቆይተውልናል፡፡

በሀገራችን ለሚስተዋሉት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮቻችን ዋነኛ መንስኤ አለመግባባታችን ነው፤ ኢትዮጵያን ሊያጠቋት ለሚሹ ኃይሎች ሁሉ በር እየከፈተ የጎዳንም ይኸው አለመግባባት ነው፡፡

የውስጥ መከፋፈላችንና በጋራ መቆም አለመቻላችን ሀብታችንን አስነጥቆን በእጃችን ያለውንም በአግባቡ መጠቀም እንዳንችል እንቅፋት በመሆን ብሔራዊ ጥቅማችንን በጋራ ማስከበር እንዳንችል ሲያግደን ቆይቷል፡፡

ለዚህም ወሳኝ መፍትሄ የሚሰጠው በውይይት ሀሳብን የመግለፅና በጋራ መፍትሄ የመፈለግ መንገድ የሆነው ሀገራዊ የምክክር መድረክ በትናንትናው ዕለት በትልቅ ተስፋ ተጀምሯል፡፡

ችግሮችን እያባበሉ ተሸክሞ ከመቆየት ይልቅ ዘላቂነት ያለው መፍትሄ መፈለግ የሚበጅ በመሆኑ ሀገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበዋል፡፡

ምክክሩ ሁሉን አካታች በመሆን ብሔር፣ ሐይማኖት፣ ጾታ፣ የኃላፊነት ደረጃዎችን ሳይለይ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ሀሳብ በነጻነት እንዲቀርብ በገለልተኝነት ዕድል የከፈተ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሀገራዊ ምክክሩ የማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ እንዳሉት፥ ለምክክሩ ውጤታማነት ከሰፈር ሀሳብ በመውጣት ለኢትዮጵያ በሚበጅ ከፍ ያለ ሀሳብ ላይ መወያየትና መግባባት ይገባል፡፡

ሀገር ለትውልዳችን የሰጠችውን ታላቅ አደራ በመረዳት፣ ከትናንት ስህተቶች ተምረንና የታሪክ ስብራቶችን ጠግነን፣ ለልጆቻችን የምናወርሳትን ኢትዮጵያ እያሰብን ስንወያይና በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮቻችንን ስንፈታ ኢትዮጵያዊ ትስስራችን ላይበጠስ ይገመዳል፡፡

በቤተልሔም ግርማ