የሀገር ውስጥ ዜና

ለሸኔ የሽብር ቡድን ሊተላለፉ የነበሩ የመገናኛ ሬዲዮዎች ተያዙ

By Yonas Getnet

July 16, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሞያሌ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በመተላለፍ ለሸኔ የሽብር ቡድን ተደራሽ ሊሆኑ የነበሩ በርካታ የመገናኛ ሬዲዮዎች ተይዘዋል አለ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፡፡

አገልግሎቱ ባደረገው የመረጃ ስምሪት ሕገ ወጥ እንቅስቃሴውን ከመነሻው ጀምሮ በቴክኖሎጂ በመታገዝ በጥብቅ ሲከታተል እንደነበር ተመላክቷል፡፡

ለሽብር ቡድኑ እንዲደርሱ ታቅደው የነበሩት የመገናኛ ሬዲዮዎቹ ከሁለት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ውለው ተገቢው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በየትኛውም የሀገሪቱ አባባቢዎች የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት የሚያውኩ ተመሳሳይ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል ከጸጥታ አካላት ጋር የተቀናጀ ስምሪት እያደረገ መሆኑን አመልክቷል፡፡

ሕብረተሰቡ በተለያየ መንገድ የሚያደርገውን ድጋፍና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም አገልግሎቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በኬንያ አዋሳኝ ቦታዎች በቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ በኩል ምዕራብ አርሲ ዞን ለሚንቀሳቀሰው የሸኔ ሽብር ቡድን ለማድረስ የታቀዱ 98 መገናኛ ሬዲዮዎችና ቻርጀሮቻቸው ከኦሮሚያ ክልል የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሚያዚያ 12 ቀን 2018 ዓ.ም በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ይታወሳል።