አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ የመርከቦችን እንቅስቃሴ እያወኩ ነው ባለቻቸው የኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ አዲስ ጥቃት ፈጸመች፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን አካሄዷን ማስተካከል አለባት በማለት ካሳሰቡ በኋላ የአሜሪካ ጦር በፈጸመው ጥቃት በሆርሙዝ ሰርጥ የመርከቦችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የኢራን ወታደራዊ ኢላማዎችን መትቻለሁ ብሏል፡፡
ኢራን በበኩሏ ባህሬን እና ኩዌትን ጨምሮ በቀጣናው በሚገኙት የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ገልጻለች፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቀናት በፊት በሰጡት አስተያየት፥ ኢራን በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ውይይት ካልተመለሰች ድልድዮችንና የኃይል ማመንጫዎችን ጨምሮ ቁልፍ መሰረተ ልማቶች የጥቃት ኢላማ እንደሚሆኑ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡
የኢራን ከፍተኛ ተደራዳሪ የሆኑት መሀመድ ባገር ጋሊባፍ በበኩላቸው፥ ሀገራቸው ከተኩስ አቁም ስምምነቱ እስካልተጠቀመች ድረስ ለስምምነቱ ተገዢ ሆና የምትቀጥልበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል።
የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ በጥቃቱ የኢራን ወታደራዊ ማዘዣ ማዕከላት፣ የአየር መከላከያ ጣቢያዎች፣ የሚሳኤል እና የድሮን መሰረተ ማከማቻዎች እንዲሁም የባህር ኃይል መከታተያ ጣቢያዎችን ኢላማ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ቴህራን በአሜሪካ የተፈጸመባትን ጥቃት ተከትሎ በባህሬን፣ ጆርዳን እና ኩዌት በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የአጸፋ ርምጃ መውሰዷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ለተወሰኑ ጊዜያት ጋብ ብሎ የነበረው የተኩስ ልውውጥ ባለፈው ሳምንት በድጋሚ ካገረሸ ወዲህ በሆርሙዝ ሰርጥ እንዲሁም በቀጣናው ያለው ውጥረት መባባሱ ነው የተገለጸው፡፡
በትዕግስት ግዛቸው