አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የልማት ዕድሎችን፣ የሰው ኃይልንና እውቀትን አቀናጅቶ በመምራት በየደረጃው ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ ይገባል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ።
ላለፉት ሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የኦሮሚያ ክልል የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት እና የፓርቲ ሥራዎች ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተጠናቅቋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ የሥራ አቅጣጫ የሰጡት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ÷ ከመደመር እሳቤ የተቀዱ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በፓርቲ፣ በመንግሥት መዋቅርና በተቀናጀ የሕዝብ ተሳትፎ እየተተገበሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም በ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ውስጥ በተጨባጭ የታየ መሆኑን ጠቅሰው÷ የተመዘገቡት ድሎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው አመራሩ በላቀ ቁርጠኝነት መንቀሳቀስ አለበት ብለዋል።
የክልሉ አመራር በሁሉም መስክ ያሉትን የልማት ዕድሎች፣ የሰው ኃይልና ዕውቀትን አቀናጅቶ በመምራት የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የተያዙ ግቦችን ለማሳካት ምቹ የልማት ዕድሎችን መጠቀም እንዲሁም የፋይናንስ አቅምና አማራጮችን ማስፋት ይገባል ነው ያሉት፡፡
በአጠቃላይ የክልሉ አመራር በአዲሱ በጀት ዓመት የልማት ዕድሎችን በሚገባ በመረዳት፣ ምርታማነትን ለማሳደግ አቅዶ መስራት፣ ተወዳዳሪነትን ሥርዓት ማስያዝ፣ ቁጠባና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት እንዲሁም የሕዝብ እና የአጋር አካላትን ሚና አቀናጅቶ መምራት እንዳለበት አስረድተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ከፊያለው ተፈራ በበኩላቸው÷ የክልሉ አመራር የብልጽግና ጉዞ ግቦችን ለማሳካት የበለጠ መትጋት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል፡፡
ያለፉት ዓመታት የብልጽግና ጉዞ በብዙ ፈተናዎች የተሞላ ቢሆንም አመራሩ ታሪክ ለመሥራት አልሞ በመንቀሳቀሱ ፈተናዎችን ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር ተችሏል ብለዋል፡፡
የተገኙ ድሎችን ለማስቀጠል በክልሉ ያለውን ሰፊ የልማት ዕድል እና የሰው ኃይል በቅንጅት በመምራት በሁሉም ዘርፍ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት የላቀ ስኬት ማስመዝገብ እንደሚገባም አሳስበዋል።