አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ላይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ማሕበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ እየመከሩ ይገኛሉ።
ከእነዚህም ውስጥ “ምንም እንኳን የመውለጃዬ ቀን ቢቃረብም “ሀገሬ ጠርታኝ አልቀርም” በማለት ከጋምቤላ ክልል ወደ አዲስ አበባ ለሀገራዊ ምክክር ጉባዔ የመጣችው ወጣት ክርኑዶ ኡጁሉ አንዷ ናት።
ወጣት ክርኑዶ ኡጁሉ በጉባዔው ሒደት ላይ እያለች በዘውዲቱ ሆስፒታል ወንድ ልጅ በሰላም ተገላግላለች።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባረፈችበት ቤት በመገኘት እንኳን በሰላም ተገላገልሽ ብለዋታል።
ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ፥ የሀገር ፍቅር እና የእኔነት ስሜት ሲኖር የማይቻል ነገር አለመኖሩን ማሳያ የሆነችውን ይህችን ጀግና እናት፤ ከጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡመድ ጋር በመሆን ባረፈችበት ቤት በመገኘት እንኳን ደስ አለሽ ብለናታል ብለዋል ።
ይህች ጀግና እናት፤ የተለመደውን ስም የማውጣት ባሕል በመተው፣ የልጇን ስም ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እንዲያወጣላት በጠየቀችው መሰረት የሕፃኑን ስም “ምክክር” ብላዋለች ሲሉም አመልክተዋል።
ዛሬም በሄድንበት ወቅት፣ ወጣቷ የመጣችበትን ታላቅ ሀገራዊ ዓላማ ለማሳካት ከጥቂት ቀናት እረፍት በኋላ ወደ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔው በልበ ሙሉነት እንደምትመለስ አረጋግጣልናለች ነው ያሉት።
ከንቲባዋ ጉባዔውን አጠናቅቃ ወደ መጣችበት እስክትመለስ ድረስ ለእሷና ለልጇ የሚያስፈልገውን ድጋፍ እናደርጋለን ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች ፥ እህታችን ወንድ ልጇን በሰላም ተገላግላ በደስታ እንደተሞላች ሁሉ፤ ኢትዮጵያ ሀገራችንም ከገጠማት አንዳንድ ችግሮች በምክክር እና በንግግር ተገላግላ፣ ትልቅ እና ወሳኝ የሽግግር ምዕራፍ እንደሚሆንላት ፅኑ እምነታችን ነው ብለዋል፡፡
ሕጻን ምክክር እና መሰል የኢትዮጵያ ሕፃናት ሁሉ ቦርቀው እና ተደስተው የሚያድጉባት እንዲሁም የሚረከቧት ሀገር ሰላሟ ሙሉ የሆነች፣ የሕዝቦች ፍቅር ያበበበት እና የበለፀገች ኢትዮጵያ እንድትሆንም ተመኝተዋል፡፡