የሀገር ውስጥ ዜና

የውድመት ሰንሰለት

By Hailemaryam Tegegn

July 17, 2026

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማዳከምና ቀጣናውን በበላይነት ለመቆጣጠር የሚፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶችና የውጭ ኃይሎች በረቀቀ መንገድ የሚከተሉት አንዱ መንገድ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የሰላምና የልማት አየር እንዳይተነፍስ ማድረግ ነው፡፡

ከአልፋሽጋ የድንበር ውጥረት በስተጀርባ ካለው ስውር እጅ ጀምሮ፣ ከካይሮ እስከ አስመራ ድረስ የተዘረጋው የሴራ ቀለበት ዋና ግቡም ይህ ነው፡፡ እሱም ጠንካራና የበለጸገች ኢትዮጵያ እንዳትኖር ማድረግና የአፍሪካ ቀንድን የዘላቂ ትርምስ ቀጣና አድርጎ ማቆየት ነው።

የጥፋት ስልታቸው መዳረሻ ቀጣናውን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ወደሌለበት የደካማ መንግሥታት ስብስብ መቀየር ሆኖ ለስኬታቸው ኢላማቸውን ኢትዮጵያ ላይ አድርገዋል፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላት መልክዓ ምድራዊ ስፋት፣ የሕዝብ ቁጥር እና የኢኮኖሚ ግዙፍነት ለቀጣናው መረጋጋት ዋነኛ ምሰሶ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን የአንቀሳቃሽነት ምሰሶ ማናጋትን ዋና ማዕከላቸው አድርገዋል፡፡

ይህን ግብ ለማሳካት እንደ ግብፅ ያሉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን የቀጣናው ሀገራት ጠንካራና ሉዓላዊ መንግሥት እንዳይኖራቸው ይፈልጋሉ። ሱዳን ለአመታት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ እንድትማቅቅ ድብቅ ድጋፍ በማድረግ፣ ደቡብ ሱዳንን ወደ ቀውስ በመክተት እና ኤርትራን እንደ ተላላኪ በመጠቀም ቀጣናውን የአቅም ቢሶች መናኸሪያ የማድረግ ጉዟቸው በተግባር የታየ ነው።

አሁን ላይ በአልፋሽጋ በኩል የሚደረገው መሰባሰብና ከበባም ግቡ የኢትዮጵያን ትኩረት በመበተን፣ ወታደራዊና የደህንነት ኃይሏን በየአቅጣጫው ማስወጠር ነው። ይህ ስልታዊ ትኩሳትን የመፍጠር አካሄድ ቀጠናውን የሽብርተኝነትና የስርዓት አልበኝነት ማዕከል በማድረግ፣ የውጭ ኃይሎች የፈለጉትን የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነት እንዲጭኑ ምቹ መንገድ ፍለጋ ነው፡፡

በአጀንዳ እጥረት የተፈጠረ ውህደት

በምንም ዓይነት መስፈርት፣ ፍላጎትና ርዕዮተ ዓለም አብረው መቆም የማይችሉ ኃይሎች በቀቢጸ ተስፋ ኢትዮጵያን ለማውደም ሲሉ በአንድነት ተሰልፈዋል። ይህ “ባልተቀደሰ ጋብቻ” የተመሰረተ መሰባሰብ የተለያየ ፍላጎት ያላቸውን የውጭ ታሪካዊ ጠላቶች እና የሀገር ውስጥ ጥቅመኛ ባንዳዎችን ያቀፈ አደገኛ ስብስብ ነው።

የውስጥ ባንዳዎች ከላኪዎቻቸው ትዕዛዝ በመቀበል በሀገር ውስጥ ትርምስና መከፋፈልን ለመፍጠር ሌት ተቀን ሲሰሩ፣ የውጭ ኃይሎች ደግሞ ቤንዚን እያርከፈከፉና እያራገቡ ለማባባስ ተዘጋጅተዋል፡፡

ይህ ሴራ የሀገር ውስጥ ሰላምን ማወክ ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድን በኢኮኖሚ፣ በኃይልና በሌሎች መሰረተ ልማቶች ለማስተሳሰር የጀመረችውን ታላቅ ጉዞ ለማጨናገፍ ያለመ ነው። ባለፉት ዓመታት በመደመር መርህ የተጠናከረው ይህ ትስስር በቀጣናው ላይ የሚፈልጉትን የበላይነት አለማግኘታቸው ለሚያሰጋቸው የሩቅ ኃይሎች ትልቅ የስጋት ምንጭ ሆኖባቸዋል። ለዚህም በቀጣናው ሀገራት መካከል የጥርጣሬና የክፋት ዘር በሚዲያዎቻቸው ይዘራሉ። በተለይም የግብፅ እጅ እስከ አስመራ ድረስ በመዘርጋት የጥፋት ተግባሩን ሁሉ ተያይዞታል፡፡

የከፋው ሴራ

የጠላቶቻችን ሴራዎች ሁሉ እጅግ ክፉው ገጽታ የምስራቅ አፍሪካ ህዝቦች ከድህነት፣ ከረሃብና ከስደት ወጥተው በራሳቸው አቅም የመልማት ያላቸውን ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብት መግፈፍ ነው። ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ለመቻልና በአረንጓዴ ዐሻራ የአር ንብረት ለውጥን ተቋቁማ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የምታደርገውን ታላቅ ብሔራዊ ጉዞ ማደናቀፍ ዋነኛ ኢላማቸው ነው።

ለዚህ ነው ጠላቶቻችን እንደ አልፋሽጋ ያሉ ለም የድንበር መሬቶችን የጦርነት ቀጣና በማድረግ፣ ምርታማነትን ማውደም እና ህዝባችን ሁልጊዜም በረሃብና በዕርዳታ ስር ተንበርክኮ እንዲኖር የሚሹት። ጠላቶቻችን እኩይ ተግባራቸውን እየፈጸሙ የሚመኙልን የምስራቅ አፍሪካ ዜጎች ሰላም አግኝተው በራሳቸው ወንዞችና ተፈጥሮ ሀብት እንዳይጠቀሙ ሲደረግ፣ ወጣቱ በቀጠናው ጦርነትና ስደት ዕጣ ፈንታው እንዲሆን ይገደዳል የሚል ነው።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ጠላቶች በአልፋሽጋም ይሁን በካይሮ የሴራ ቀለበት በኩል የሚሸርቡት ድር የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለመግፈፍና የቀጠናውን ህዝቦች የልማት ተስፋ ለማጨናገፍ ያለመ ነው፣ ሆኖም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት የዚህን ጂኦፖለቲካዊ ቁማር መርዛማነትና ድብቅ ዓላማ በሚገባ ይረዳሉ። መረዳት ብቻ ሳይሆን እንደቀደሙት ሁሉ ያከሽፉታል፡፡

ኢትዮጵያ የዘመናት ታሪካዊ ቁስሎቿን በሀገራዊ ምክክር ለመፍታት የጀመረችው ጉዞ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፍፃሜ እና የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት የጽናታችን ህያው ምስክሮች ናቸው። በመሆኑም አልፋሽጋም ሆነ ሌሎች ድንበሮቻችን የጥፋት ኃይሎች የሴራ ሰሌዳ መሆናቸው አብቅቶ፣ የሉዓላዊነታችን መከበሪያና የታሪካዊ አንድነታችን ማሳያ ሆነው ይቀጥላሉ። በኢትዮጵያና በቀጠናው ህዝቦች የጋራ ጥንካሬም የጠላቶቻችን የውድመት ሰንሰለት መበጠሱ የማይቀር እውነት ነው።