ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ ለስድስተኛ ምሽት በኢራን ላይ ከፍተኛ ጥቃት ፈፀመች

By Abiy Getahun

July 17, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የስምምነት ጠረጴዛቸውን ገልብጠው ዳግም ወደ ግጭት የገቡት ዋሽንግተን እና ቴህራን ግጭታቸው ተባብሶ ቀጥሏል።

በዚህም አሜሪካ በኢራን ላይ እየፈጸመችው ያለው ጥቃት ለስድስተኛ ምሽት ቀጥሎ ከፍተኛ ጥቃት ፈጽማለች።

በደቡባዊ ኢራን የባንዳር አባስ ባለስልጣናት እንደገለፁት፤ የኃይል ማመንጫዎች እና የባቡር ጣቢያዎችን ጨምሮ የሲቪል መሠረተ ልማቶች የጥቃቱ ዒላማ ሆነዋል።

ሁለቱም ወገኖች የሆርሙዝ ሰርጥን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ትግል ላይ ሲሆኑ፤ አሜሪካ በኢራን ላይ ተከታታይ ጥቃቶችን እየፈፀመች ነው።

የአሜሪካ ማዕከላዊ ማዘዣ (ሴንትኮም) በበኩሉ፤ ጥቃቱ የኢራን ወታደራዊ አቅምን የበለጠ ለማዳከም ያለመ እንደሆነ አስታውቋል።

የኢራን የመንግሥት ሚዲያዎች፤ አሜሪካ ድልድዮችን፣ የባቡር ጣቢያን እና አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ ሌሎችም የሲቪል መሠረተ ልማቶችን መትታለች ሲሉ ዘግበዋል።

ቢቢሲ በበኩሉ በሆርሞዝጋን ግዛት ከባንዳር አባስ በስተ ምዕራብ በሚገኝ ድልድይ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

ለአሜሪካ ጥቃት ምላሽ በኳታር በባህሬን እና ሌሎችም አካባቢዎች ያሉ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮችን እየመታች የምትገኘው ኢራን በኳታር በፈፀመችዉ ጥቃት አንድ ታዳጊ ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል የዋሽንግተን እና ቴህራን ዳግም መካረር አዝማሚያ ያላማራቸው ቻይና እና ፓኪስታን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው በኩል ዳግም የሰላም ንግግሩ እንዲጀምር ጥሪ አቅርበዋል።

በእመቤት ሲሳይ