የሀገር ውስጥ ዜና

የመደመር መንግሥት ሰው ተኮር የልማት ስራዎች

By Abiy Getahun

July 17, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ዓመታት የመደመር መንግሥት ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድሎችን ከማስመዝገቡም በላይ በሰው ተኮር ልማቶች የሰራው ስራ በልዩነት ይነሳል፡፡

የመደመር መንግሥት በግብርና፣ በቱሪዝም እና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ተጨባጭ ስኬቶች ያስመዘገበ ሲሆን፤ በማሀበራዊ ዘርፉም በሰው ተኮር ስራዎች አንጸባራቂ ውጤቶችን አምጥቷል፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ በመደመር መንግሥት እሳቤ እንደ ሀገር ተከታታይ የሚባል ልማት እና የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ችላለች፡፡

ይሄ እድገት የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል፣ የዜጎችን የስራ ዕድል ፈጠራ እና ተጠቃሚነት እውን በማድረግ እንዲሁም ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ አስችሏል፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በጤናው መስክ በርካታ የጤና ተቋማትን በሁሉም የሀገሪቱ አከባቢዎች በመገንባት እንዲሁም ዘመናዊ የጤና ቁሳቁሶችን ከውጪ በማስገባት ዘርፉን ለማዘመን እና አገልግሎቱን ለማሳደግ ከፍተኛ ስራ ተሰርቷል፡፡

በትምህርት ዘርፍ የትምህርት ጥራትን ለማሳደግና የበቃ ዜጋን ለማፍራት በተደረገው ጥረት ከ30 ሺህ የሚልቁ መዋዕለ ህጻናት የተገነቡ ሲሆን፤ ይህም ህጻናት ላይ ትኩረት በማድረግ ብቁ ዜጋ ለመፍጠር ያስችላል።

በተጨማሪም የመማር ማስተማር ሒደቱን በማሻሻል እንዲሁም የፈተና አሰጠጥ ሂደትን በማዘመንና ኩረጃን በማስቀረት የነጠሩ ተማሪዎች ብቻ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን እንዲቀላቀሉ ማድረግ ተችሏል፡፡

በኮሪደር ልማት ስራ ከተሞች ያደገ ሀገር ቁመና እንዲላበሱ ከማስቻሉም በላይ ዜጎች በነጻነት እና ጤናቸው በተጠበቀ መልኩ ኑሯቸውን እንዲገፉ ተደርጓል።

በግብርና በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በዓመት ሁለት ሶስቴ ማምረት ተችሏል፤ ዘመናዊ የእርሻ ማሽነሪዎችን በመጠቀም ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ አድጓል።

በኋላ ቀር መንገድ በበሬ በማረስ ላይ ብቻ ተወስኖ የነበረው የእርሻ ስራ ወደ ሜካናይዜሽን በፍጥነት እየተሸጋገረ ሲሆን፤ በዝናብ ላይ የተንጠለጠለው ግብርና በመስኖ ጭምር እየተሰራበት በመሆኑ ብዙዎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሁለትና ሶስት ጊዜ የሚያመርቱ ሆነዋል።

ይህ ሁኔታ የአርሶ አደሩን ገቢ በማሳደግ ኑሮውን እያሻሻለ መጥቷል። በገጠር ኮሪደር ስራ የአርሶና አርብቶ አደሩን አኗኗር የማዘመን ተግባር በስፋት እየተከናወነ ተስፋ ሰጪ ውጤት ተመዝግቧል።

በቱሪዝም ዘርፍ በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች በተሰሩ ዘመናዊ ሪዞርቶች የየአካባቢዎቹ ልማት እደገት ዕውን ከመሆኑም በላይ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ጨምሯል። ዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል።

በአቤል ነዋይ