የሀገር ውስጥ ዜና

 የ4 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር የትምህርት ዕድል አሸናፊው ተማሪ ኃይሌ አዳነ

By Mikias Ayele

July 18, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ4 ነጥብ 1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የነፃ ትምህርት ዕድል ተወዳድሮ በማሸነፍ 11 የአሜሪካ ታዋቂ ዩኒቨርሲቲዎች መግባት መቻሉን ያረጋገጠው ተማሪ ኃይሌ አዳነ ትውልድ እና እድገቱ በአሶሳ ከተማ ነው።

የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በአሶሳ ከተማ የተከታተለው ተማሪ ኃይሌ፤ ያገኘው ዕድል በዓለም ላይ ለመግባት እጅግ በጣም ከባድ ውድድር የሚጠይቁ እና የዓለምን ታሪክ የቀየሩ ሰዎችን ያፈሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ናቸው።

ተማሪ ኃይሌ ነፃ የትምህርት ዕድል ካሸነፈባቸው ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ፣ ፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ እና ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፔንስልቬንያ ይገኙበታል።

ከቅዳሜ ማለዳ ፋና 90 ጋር ቆይታ ያደረገው ተማሪ ኃይሌ በራሱ ተነሳሽነት የተለያዩ የኦንላይን አማራጮችን በመጠቀም ዌብዴቨሎፕመንት ይማር እንደነበር ተናግሯል።

የክረምት ወቅትን አዳዲስ ክህሎቶችን ለመማር ባለው ጉጉት በአዲስኮደር የኮዲንግ ስልጠና በሀገር ውስጥ፤ ቲኤኤስኤስ እና ዋይዋይኤኤስ የተሰኙ ፕሮግራሞችን ደግሞ በአሜሪካ እና ዚምባቡዌ ተከታትሏል።

የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሰመር ካምፕ ስልጠናም በዘርፉ ልምድ ያላቸው መምህራን ከመሰረታዊ ጽንሰ ሀሳብ ጀምሮ እስከ የተለያዩ ደረጃዎችን በማለፍ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂዎችን በግልጽ እና በተግባር ቀስሟል።

ኃይሌ እና ጓደኞቹ ያገኙትን ዕውቀት በመጠቀም የአየር ንብረት ድርቅን የመጪዎቹን 6 ወራት አስቀድሞ በ95 በመቶ ትክክለኛነት ደረጃ መተንበይ የሚችል የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሞዴል አበልጽገዋል።

የዌብዴቨሎፕመንት ክህሎቱን ከየአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር በማዋሃድ (ethioexam.et) የተሰኘ ተማሪዎች ለሀገር አቀፍ ፈተና እንዲዘጋጁ የሚረዳ የትምህርት መተግበሪያ ያበለጸገ ሲሆን፤ መተግበሪያው ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያገለገለ ይገኛል፡፡

የ19 ዓመቱ የኃይሌ ታሪክ በሀገራችን ለሚገኙ ተማሪዎች በትጋት ከሰሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደርና ማሸነፍ እንደሚችሉ ማረጋገጫ ነው።

ለኮምፒውተር እና ለቴክኖሎጂ ከፍተኛ ፍቅር ያለው ኃይሌ የመጨረሻ ምርጫውን በዓለም ላይ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ቁጥር አንድ በሆነው ማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ በማድረግ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ትምህርቱን ይጀምራል።

በመጪው ሐምሌ ወር ወደ አሜሪካ በመጓዝ መላው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ይወክላል።

በሄኖክ ለሜ