የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ለአፍሪካ እና ለዓለም የሚተርፍ ነው

By Yonas Getnet

July 18, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋምና የተራቆቱ መሬቶችን ለማልማት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረ ታላቅ የችግኝ ተከላ ሀገራዊ እንቅስቃሴ ነው።

ዓላማው የሀገሪቱን የደን ሽፋን ማሳደግ፣ በረሃማነትን መከላከል እና ለምግብ ዋስትና አስተዋጽኦ ማድረግ ነው።

በአንድ ወቅት ከ40 በመቶ በላይ የደን ሽፋን እንደነበራት ይነገርላት የነበረችው ኢትዮጵያ በወቅቱ በነበረው ዘላቂ ያልሆነ የተፈጥሮ ሃብትና የመሬት አጠቃቀም ምክንያት የደን ሽፋናችን ወደ 3 በመቶ ወርዶ ነበር፡፡

የብዝሃ ሕይወት መመናመን በተለይም የመሬት መደህየት እና ምርታማነት መቀነስ እንዲሁም የውሃ አካላት በደለል መሞላት ማህበረሰቡን ለከፋ ድርቅ፣ ለጎርፍና ለምግብ ዋስትና ችግሮች ተጋላጭ አድርጎት እንደቆየ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የተፈጥሮ ሃብት መመናመን ተከትሎ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን አደጋ ለመከላከል እና የተፈጥሮ ሃብትን ለመጠበቅ አረንጓዴ ዐሻራ አማራጭ የሌለውና ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የደን መጨፍጨፍ በመከላከልና የአየር ሁኔታን በማሻሻል የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ አረንጓዴ ኢኮኖሚን በመገንባት የወደፊት መልካም ዕጣ ፈንታን የሚያሳይ መሰረት እየጣለ ይገኛል፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በግብርናው ዘርፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት እንዲጨምር በማድረግ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ዘላቂ ተጠቃሚነትን አስገኝቷል፡፡

በተጨማሪም እንደ ሀገር ወጣቶችና ሴቶች ችግኝ በማፍላትና በመንከባከብ በስፋት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው፡፡

ችግኞች መተከላቸው በቂ ዝናብ እንዲዘንብ እና የአካባቢ ሥነ ምህዳርን ለመጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡

መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ በዓለም ትልቁ ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ልማት መርሐ ግብር የሚተገበርባት ሀገር እንድትሆን በማድረግ ሌሎች ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ለሚያደርጉት ጥረት አርአያ ሆኗል፡፡

በዚህም የአየር ንብረት ለውጥ ዲፕሎማሲን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና አለው፡፡

የዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በትዕግስት ግዛቸው