የሀገር ውስጥ ዜና

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመደመር መንግሥት እይታ

By Melaku Gedif

July 19, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ”መደመር” እሳቤ የትብብር፣ የመተማመን፣ የአንድነትና የጋራ ኃላፊነት መርህን በማጠናከር የሀገር ግንባታን ለማፋጠን የሚያበረታታ ነው።

በዚህ ረገድ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የመደመርን ፍልስፍና በተግባር ከሚያሳዩ ዋና መንገዶች አንዱ ነው።

በመደመር እሳቤ መሠረት በመንግሥት፣ በወጣቶች፣ በሴቶች፣ በሲቪል ማኅበራትና በመንግሥታዊ ተቋማት ትብብር የተለያዩ የበጎ ፍቃድ ሥራዎች ተከናውነዋል።

ለአብነትም በክረምት የበጎ ፍቃድ መርሐ ግብሮች በመላ ሀገሪቱ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትንና የህዝብ አገልግሎት ተቋማት እድሳት ስራዎች ይጠቀሳሉ።

በተጨማሪም በዚሁ የበጎ ፍቃድ ተግባር በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን እንዲሁም የአካባቢ ጽዳት፣ የወንዝ ማጽዳት፣ የቆሻሻ ማስወገድና የሕዝብ መገልገያ ቦታዎችን የማስዋብ ሥራዎች በበጎ ፍቃደኞች ተከናውነዋል።

ለአረጋውያን፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብ፣ የልብስና የመኖሪያ ድጋፍ እንዲሁም የደም ልገሳ በሰፊው ሲከናወን ቆይቷል።

ለተማሪዎችና ለትምህርት ቤቶች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ የትምህርት ቤት እድሳትና የቤተ መጻሕፍት ማደራጀት የመሳሰሉ ተግባራት በወጣት በጎ ፈቃደኞች ተከናውነዋል።

መደመር የልዩነትን ኃይል ወደ ጋራ ጥቅም የሚቀይር እሳቤ ሲሆን፥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ይህንን እሳቤ በተግባር ያንጸባርቃል።

ዜጎች ዕውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በማዋሃድ የማኅበረሰብን ችግሮች በጋራ ሲፈቱ የአንድነት መንፈስ ይጠናከራል፣ የመተማመን ባህልም ይጎለብታል።

በመደመር መንግሥት የበጎ ፍቃድ መርሐ ግብሮች ውስጥ ወጣቶች ዋነኛ ተዋናዮች ናቸው።

በአካባቢ ጥበቃ፣ በትምህርት ድጋፍ፣ በጤና ግንዛቤ፣ በሰብዓዊ ድጋፍና በማኅበረሰብ ልማት ሥራዎች ያደረጉት ተሳትፎ የሀገር ግንባታን በእጅጉ ማገዝ ችሏል።

በመደመር መንግሥት ዘመን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከግለሰብ ተሳትፎ ባለፈ የሀገራዊ እንቅስቃሴ መልክ ይዞ እየተከናወነ ይገኛል።

በተለይ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር፣ የክረምት የበጎ ፍቃድ ዘመቻዎች፣ የደም ልገሳ፣ የአካባቢ ጽዳት፣ ለተጎጂዎች የተደረጉ ድጋፎችና የትምህርት ቤቶች እድሳት የመደመር እሳቤን በተግባር ያሳዩ ዋና ዋና ምሳሌዎች ናቸው።

ይህ የበጎ ፍቃድ ባህል በቀጣይነት ተጠናክሮ ሲቀጥል ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት፣ ለማኅበራዊ አንድነትና ለሀገራዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

በአመለወርቅ ደምሰው