የሀገር ውስጥ ዜና

በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ 11 ነጥብ 7 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ይጠበቃል

By Melaku Gedif

July 19, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በ2019 በጀት ዓመት 11 ነጥብ 7 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ይጠበቃል አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፡፡

የጨፌ ኦሮሚያ 5ኛ ዓመት 6ኛ የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባዔ በአዳማ ጨፌ አዳራሽ እየተካሄደ ነው፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ በዚህ ወቅት ÷ የኦሮሚያ ክልል ኢኮኖሚ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በተከታታይ እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሰረትም ክልሉ በ2019 በጀት ዓመት 11 ነጥብ 7 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚያስመዘገብ መተንበዩን አመልክተዋል።

ከዚህም ውስጥ የኢንዱስትሪ ዘርፉ በ23 ነጥብ 7 በመቶ፣ ግብርናው በ8 ነጥብ 6 በመቶ እና የአገልግሎት ዘርፉ በ9 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚያድጉ ይጠበቃል ብለዋል።

የ2019 የበጀት ዓመት እቅድ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረጉ ጥናቶች ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተናግረዋል።

በ2018/19 ዓ.ም በጸደይ ወቅት ግብርና 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ሔክታር መሬት ለማልማት እና 46 ነጥብ 2 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በክረምት እርሻ ወቅት ደግሞ 12 ነጥብ 35 ሚሊየን ሔክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ393 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል ለ2 ነጥብ 86 ሚሊየን ወጣቶች ቋሚ የሥራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል፡፡

በእዮናዳብ አንዱዓለም