በአፍሪካ ቀንድ የጂኦ-ፖለቲካዊ መድረክ ላይ ከሰሞኑ እጅግ አስቂኝ የሆነ ቴአትር ለእይታ በቅቷል።
የመድረኩ ስያሜ “የአስመራው ቤተ-መንግሥት” የተሰኘ ሲሆን ፤ የድራማው አዘጋጅ፣ ስክሪፕት ጸሐፊና የፋይናንስ ስፖንሰር ደግሞ ካይሮ ነች።
በዚህ የፖለቲካ አሻንጉሊቶች ትዕይንት ላይ በዋና ተዋናይነት የተሰለፉት የሱዳን ጦርነት አቀጣጣይ ጄኔራል አብደልፋታህ አል-ቡርሃን እና የኤርትራው ብቸኛ ሰው አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ናቸው።
የዚህ ቴአትር አስቂኝና አሳዛኝ ገፅታ የሚጀምረው፤ በእብደት ከተሞላው የተዋንያዎቹ መራራ እውነታ ነው።የገዛ ቤታቸውን አቃጥለው፤ የሚሞቁትን እነዚህን ግለሰቦች እንደ ሀገር መሪ አድርጎ ማሰብ ለፖለቲካ ሳይንስ ትልቅ ስላቅ ነው። ሁለቱም መሪዎች ሳይሆኑ የቀጣናው የብጥብጥ እና የጦርነት ኮንትራክተሮች ናቸው።
• ጄኔራል አል-ቡርሃን፦
በካርቱም የገዛ ቤተ-መንግሥታቸውን ማስከበር አቅቷቸው፣ ሱዳንን ወደ ፍርስራሽነትና ወደ እርስ በርስ እልቂት የገፉ ሰው ናቸው። የገዛ ሕዝባቸውን በሚሊየኖች አፈናቅለው በረሃ ላይ ጥለው፣ በአስመራ ስለ “ቀጣናዊ ደህንነት” ሲለፍፉ መስማት የዓመቱ ትልቅ የፖለቲካ ቀልድ ነው። የገዛ ቤቱ በእሳት እየነደደ ያለ ሰው የጎረቤቱን ቤት ሰገነት ለመጠገን ሲሞክር ማየት ምንኛ አስቂኝ ነው?
• አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ፦
በሌላኛው የድራማው ጥግ ያሉት እኚህ ግለሰብ ደግሞ ሀገራቸውን ኤርትራን ከዓለም ነጥለው ወደ አንድ ትልቅ ወታደራዊ እስር ቤት የቀየሩ የጥፋት ኢንጅነር ናቸው። የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ደም ስር የበጠሱ፣ ወጣቱን ትውልድ በግዴታ ውትድርና እያሰቃዩ ሀገሩን ጥሎ እንዲሰደድ ያደረጉ ሰው፣ አሁንም በአካባቢው “ተፅዕኖ ፈጣሪ” መስለው ለመታየት የሱዳንን ቀውስ ለራሳቸው የፖለቲካ ቁማር መጠቀሚያ ለማድረግ፤ ባረጀና ባፈጀ ሴራ ድራቸው ይውተረተራሉ፡፡
እነዚህ የጥፋት አበጋዞች በሀገራቸው ፍርስሽ ላይ ቆመው፣ ከካሜራ ፊት ጥርሳቸውን በፈገግታ ሲገልጡ፣ ከጀርባ ሆና ልጓማቸውን የምትጎትተውና ስክሪፕታቸውን የምታቀብላቸው ካይሮ መሆኗ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
ዋናው የቴአትሩ መልዕክት ግልፅ ነው፡፡እነዚህ አካላት የራሳቸውን ሀገር ያፈረሱና ያዳከሙ የግብጽ ተላላኪዎች (Proxies) ናቸው። ካይሮ በቀጣናው በኩል የጦር መሳሪያ በማከማቸትም ሆነ እነዚህን ሀይል አፍራሾች በአስመራ በማሰባሰብ፣ የኢትዮጵያን ቀጣናዊ የበላይነት ለመቀልበስና የሕዳሴውን ግድብ ስኬት ለማጨለም የ”እጅ አዙር ጦርነት” (Proxy War) አጀንዳዋን እያስፈጸመች ነው።
ጄኔራሉና አቶ ኢሳያስ የራሳቸው ፖለቲካዊ ህልውና የሌላቸው፣ ግብፅ ቀጣናውን ለማተራመስ የተከራየቻቸው አፍራሾች መሆናቸውን በሚገባ አረጋግጠዋል።
ይህ ሁሉ የከሰሩ መሪዎች ልፊያ ግን፣ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ብስለት እና ጽኑ መሰረት ጋር ሲነፃፀር ትርጉም አልባ የውሃ ላይ ኩፋፌ ነው። የካይሮ ተላላኪዎች በአስመራ የጥፋት ዳንኪራ በሚረግጡበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የሰራችው ነገር ቢኖር እጅግ አስገራሚ የፖለቲካ ብስለት ማሳየት ነው። ከስሜት በስሌት፣ ከድንፋት በግንባታ ላይ በማተኮር፤ ለጩኸታቸው ጆሮ ሳትሰጥ፦
• የውስጥ ምክክሯን አጠናክራለች፣
• ተቋማዊ ግንባታዋን እያሳደገች ትገኛለች፣
• የቀጣናውን የሰላምና የልማት አጀንዳ እንደ አንድ ኃላፊነት የሚሰማው ቀጣናዊ መሪ በብስለት እየመራች ነው።
የኢትዮጵያ ጥንካሬ የሚመነጨው ብሔራዊ ሉዓላዊነትን ከጥቅም ባስከበረና ሕዝባዊ መሰረት ባለው ፖለቲካዊ ቁመናዋ ነው።
ዜሮ ሲደመር ዜሮ በሒሳብ ስሌቱ ዜሮ እንደሆነ፤ ሁለት ባዶ እጆች ሲጨባበጡ ምንም ረብ ያለው ነገር እንደማይለዋወጡም እንዲሁ፡፡
ሀገራቸውን ያፈረሱ የሁለት የብጥብጥ ፈጣሪዎች ባዶ እጅ መያያዝም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ አንዳችም ተፅዕኖ ሊያሳድር አይችልም።
የካይሮ ፈረሶች በአስመራው መድረክ ላይ ተገናኝተው የጥፋት ድቤ ቢመቱም፣ ሁለተናዊ ብሔራዊ አቅሟን በአለት ላይ እየገነባች ወደፊት የምትጓዘውን ኢትዮጵያን ማናወጥ ከቶም አይችሉም።