የሀገር ውስጥ ዜና

የምክክር ጉባኤው ተሳታፊዎች በተመደቡበት አጀንዳ ላይ መመካከር ጀምረዋል – ኮሚሽኑ

By Hailemaryam Tegegn

July 20, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ተሳታፊዎች በተመደቡበት አጀንዳ ላይ በዛሬው ዕለት መመካከር ጀምረዋል አለ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ፥ ዛሬ የተጀመረው ሂደት የምክክሩ ቁልፍ አካል መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ተመካካሪዎች በንዑስ ቡድኖች ተከፋፍለው በተመደቡበት አጀንዳ ላይ መመካከር መጀመራቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

የተጀመረው የምክክር ሂደት ተመካካሪዎች ሀሳባቸውን የሚያንሸራሽሩበትና የሌሎችን አመለካከት የሚያደምጡበት ቁልፍ ምዕራፍ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

ተመካካሪዎቹ በተመረጡት አጀንዳዎች ላይ ተመድበው የቅድመ ምክክር ውይይቶችን፣ ትውውቆችን እንዲሁም በምክክሩ የአሰራር ስርዓቶች ላይ በቂ ግንዛቤ ወስደዋል ብለዋል፡፡

በዚሁ መሠረት በዛሬው ዕለት ተመካካሪዎች በንዑስ ቡድኖች በመከፋፈል በተመደቡበት አጀንዳ ላይ መመካከር ጀምረዋል ብለዋል፡፡

በአንድ አጀንዳ ላይ 500 ተመካካሪዎችን የያዘ አብይ የስራ ቡድን መዋቀሩን ጠቅሰው፥ በእነዚህ አብይ ቡድኖች ስር እያንዳንዳቸው 50 ተመካካሪዎች ያሏቸው 10 ንዑስ ቡድኖች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ 80 ንዑስ ቡድኖች በተመደቡላቸው አጀንዳዎች ላይ እየመከሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ሂደቱ በስኬት እንዲከናወን ኮሚሽኑ በስራ ልምዳቸውና በትምህርት ዝግጅታቸው አንቱታን ያተረፉ 160 የሚሆኑ አመካካሪዎችን መመደቡን አመልክተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም 256 የሚሆኑ የቃለ ጉባኤ ጸሃፊዎች ተሰማርተው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን በብቃት እየመሩ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡

በዮናስ ጌትነት