የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያን ሰላም መንሳትም ሆነ ሕጋዊና ስትራቴጂካዊ የባህር በር መንፈግ አይቻልም

By Abiy Getahun

July 20, 2026

የኢትዮጵያ የፀጥታ መዋቅር የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስከበር አስተማማኝ አቅም ፈጥሯል፡፡

ከህዝባዊ አንድነት እና ከዲፕሎማሲያዊ ቁርጠኝነት ጋር ተዳምሮ መዋቅሩ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ የኢኮኖሚ ህልውናን እና ሙሉ ብሔራዊ ጥቅሞች የሚያረጋግጥ ኃይል ሆኖ ተገንብቷል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የደኅንነት ተቋማት በቴክኖሎጂ፣ በሰው ሃይል እና በስልጠና የዳበሩ በመሆናቸው ማንኛውንም አይነት የውስጥና የውጭ የደኅንነት ስጋት የመቀልበስ ሙሉ ብቃት አላቸው።

ተቋማቱ የሀገሪቱን ሰላም በዘላቂነት ለመጠበቅ የሚያስችል ስልታዊ ዝግጁነት ያላቸው በመሆኑ፣ የውስጥ አለመረጋጋትን ለመፍጠር የሚሰሩ ስልቶችን ሙሉ በሙሉ ማክሸፍ ችለዋል።

ኢትዮጵያ የገነባቻቸው ተቋማት የራሷን ሰላም ከማስከበር ባለፈ፣ በአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

130 ሚሊዮን ህዝብ ያላት እና በከፍተኛ ፍጥነት የምታድግ ሀገር የባህር በር ማግኘቷ የቅንጦት ሳይሆን የኢኮኖሚ ህልውና እና ብሄራዊ ደኅንነት ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት በጉልበት ሳይሆን የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እና ቀጣናዊ ትስስርን መሠረት ያደረገ ህጋዊ መንገድ ነው።

ሀገሪቱን የባህር በር በመንፈግ በኢኮኖሚ ለመጫንና ለማዳከም የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ጫናዎች በኢትዮጵያ የጸና አቋም እና በተቋማቱ ጥንካሬ ምክንያት ሊሳኩ አይችሉም።

የደኅንነት ተቋማቱ ጥንካሬ የሚመነጨው ከህዝብ ጥንካሬ በመሆኑ፣ በሀገራዊ ደኅንነት ጉዳይ ላይ የሚንጸባረቀው የአንድነት መንፈስ ለማንኛውም ሴራ የማይበገር ክንድ ሆኗል።

የኢትዮጵያ የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋማት የሀገሪቱን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ የጠበቁ በመሆናቸው፣ ሀገሪቱን ሰላም የመንሳትም ሆነ ወደ ባህር የመውጣት ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ መብቷን የመግታት ሙከራዎች ሁሉ ከንቱ ሆነው ይቀራሉ።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር የምታደርገውን ጉዞ ለማደናቀፍ እና በውስጥ ሰላምን ለመንሳት ከባንዳዎች ጋር በመቀናጀት ይንደፋደፋሉ፡፡

ይህ ከቅዠትነት አልፎ የሚሳካ ፍላጎት አይደለም፡፡

ነገር ግን ጠንካራና ዘመናዊ የፀጥታ እና የደኅንነት ተቋማት የገነባችውን ኢትዮጵያን ሰላም መንሳትም ሆነ ሕጋዊና ስትራቴጂካዊ የባህር በር የመንፈግ ሴራ በፍጹም አይቻልም፡፡