የሀገር ውስጥ ዜና

አሜሪካ በኢራን ላይ ጠንካራ ጥቃት ሰንዝራለች – ፕሬዚዳንት ትራምፕ 

By Mikias Ayele

July 20, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ትናንት ምሽት ጠንካራ የተባለ ጥቃት መሰንዘሯን ተናገሩ።

በኢራን ላይ የተወደው ጠንካራ ርምጃ የአሜሪካ ሶስት ወታደሮች በኢራን ጥቃት በመገደላቸው እንደሆነ ተገልጿል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በኢራን ላይ የሚሰነዘረዉ ጥቃት በጣም እንዲጠናከር ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውም ተመላክቷል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፤ በቅርቡ በደረሰ ጥቃት የአሜሪካ በዮርዳኖስ ሁለት ወታደሮች እና በኢራቅ ውስጥ ደግሞ አንድ ወታደር ህይወታቸውን አጥተዋል።

ዛሬም ቀጥሎ ባለው የአሜሪካ ጥቃት በኢራን በርካታ አካባቢዎች ፍንዳታ እየተሰማ ሲሆን፤ በዚህ ሳቢያም የተዘጉ ስራዎች መኖራውን እና ሰራተኞች ስራ እንዳይገቡ መደረጉን ነው ቢቢሲ ያስነበበው።

አሜሪካ ቴህራን በሆርሙዝ ሰርጥ በሚተላለፉ መርከቦች ላይ የምታደርሰውን ጥቃት ለመግታት እንዲቻል ወታደራዊ ቦታዎችን እና የመገናኛ አውታሮችን ዒላማ አድርጋ እያጠቃች ነው።

በሁለቱ ወገኖች መካከል ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት ማብቃቱ ከተገለጸ ወዲህ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት 9ኛ ምሽቱን አስቆጥሯል።

ጥቃቱን አስመልክቶ የኢራኑ ታስኒም የዜና ወኪል እንደዘገበው ታብሪዝ፣ ቻባሃር፣ ኮናራክ፣ ባንዳር ማህሻህር እና ባንዳር ኢማምን ጨምሮ በተለያዩ የኢራን ከተሞች ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

የአሜሪካ ጥቃት እስከቀጠለ ድረስ በሆርሙዝ ሰርጥ ምንም ዓይነት ነዳጅ እንደማያልፍ የኢራን አብዮታዊ ዘብ አስጠንቅቋል፡፡

በእመቤት ሲሳይ