አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ኅብረት የትምህርት ክፍል ኃላፊ ሶፊያ አሺፓላ የኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ የማቋቋም ርዕይ ሀገሪቱን የአፍሪካ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ማዕከል የሚያደርግ ታሪካዊ እርምጃ ነው አሉ።
ኢትዮጵያ ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ ውጤት ባለቤት ለመሆን እና ዜጎችን ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ለማስተሳሰር የተለያዩ ስራዎችን እየሰራች ትገኛለች፡፡
ከእነዚህ ስራዎች መካከል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ሲሆን፤ ዩኒቨርሲቱውን ለአገልግሎት ለማብቃት ትኩረት ተሰጥቷል።
የአፍሪካ ኅብረት የትምህርት ክፍል ኃላፊ ሶፊያ አሽፓላ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ መስክ ወሳኝ መደላድል በመፍጠር አበረታች ውጤት እያመጣች ነው።
የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂና የአምስት ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ መርሐ ግብር የዜጎችን የዲጂታል፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎትና የዳታ ሳይንስ ዕውቀትና ክህሎት አቅም እያሳደጉ እንደሆነም ተናግረዋል።
በተለይም የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ልማት ለማፋጠን ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም ኢትዮጵያ የወሰደችው ተነሳሽነት ከፍተኛ አድናቆት የሚቸረው ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተጀመረው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ልማት አብዮት በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተመሳሳይ ኢንቨስትመንቶች እንዲስፋፉ በር የሚከፍት ታሪካዊ ክስተት እንደሆነም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ የማቋቋም ርዕይ የወደፊቱን ትምህርትና ምርምር በተሻለ ጥራት በመቅረጽ ሀገሪቱን ፈር ቀዳጅ እንደሚያደርጋት ሶፊያ አሽፓላ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የትምህርት መሠረተ ልማትን የማስፋፋት ተግባር የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን በማረጋገጥ ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር በአርአያነት የሚወሰድ መሆኑም ተብራርቷል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።