የሀገር ውስጥ ዜና

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ቁልፍ ምዕራፍ ውይይት በይፋ አስጀመረ

By Yonas Getnet

July 20, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በ80 ንዑስ ቡድኖች ያደራጀው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የውይይት ምዕራፍ በዛሬው ዕለት በይፋ መጀመሩን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር እንዳሉት÷ የተጀመረው የንዑስ ቡድን ውይይት የሀገራዊ ምክክሩ ቁልፍ ምዕራፍ ነው።

ምዕራፉ ተመካካሪዎች በተመደቡባቸው አጀንዳዎች ላይ ሐሳባቸውን የሚያቀርቡበትና አንዱ የሌላውን ሐሳብ በማዳመጥ በሰለጠነ መንገድ የሚመካከሩበት ሂደት እንደሆነም ገልጸዋል።

ለእያንዳንዱ አጀንዳ 500 ተመካካሪዎችን ያካተተ ዐቢይ የሥራ ቡድን መደራጀቱንም አብራርተዋል።

እያንዳንዱ ዐቢይ የሥራ ቡድን 50 ተመካካሪዎች ያሉባቸው 10 ንዑስ ቡድኖችን የያዘ መሆኑን ገልጸው÷ በአጠቃላይ 80 ንዑስ ቡድኖች በተመደቡላቸው አጀንዳዎች ላይ ዝርዝር ውይይት እያካሄዱ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ተመካካሪዎቹ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በኮሚሽኑ ይፋ በተደረጉት ስምንት አጀንዳዎች ላይ ተመድበው የቅድመ ምክክር ውይይቶችን፣ የጋራ ትውውቆችን እና በምክክሩ የአሠራር ሥርዓቶች ላይ አስፈላጊውን ግንዛቤ ወስደዋል ነው ያሉት።

የውይይቱን ሂደት በተደራጀ መልኩ ለማስተባበር ኮሚሽኑ በሥራ ልምድና በትምህርት ዝግጅት ብቃት ያላቸውን 160 አመካካሪዎች እና 256 የቃለ ጉባኤ ጸሐፊዎች ማሰማራቱን ተናግረዋል።

ባለሙያዎቹ የምክክሩን ሂደት የመመዝገብና የመደገፍ ሥራቸውን እያከናወኑ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።