አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካና የባሕረ ሰላጤውን ሀገራት ስትራቴጂክ የኢኮኖሚ አጋርነት ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየሰራች ነው አለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡፡
የአፍሪካና የባሕረ ሰላጤው ሀገራትን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ሀደራ አበራ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የአፍሪካና የባሕረ ሰላጤው ሀገራት ስትራቴጂክና ዘላቂ አጋርነት የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።
በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ ሽግግር ምዕራፍም በዓለም ላይ በፍጥነት ከሚያድጉ 15 ኢኮኖሚዎች መካከል ሰባቱ በአህጉሪቱ እንደሚሆኑ ይጠበቃል ብለዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነትም ግዙፍ የዓለም አቀፍ የንግድ ቀጣና በመፍጠር ለኢንዱስትሪ፣ ለንግድና ለኢንቨስትመንት አዳዲስ ዕድሎችን እየከፈተ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም አፍሪካ የኢንቨስትመንት መዳረሻነቷን በማስፋት የምግብ ዋስትና፣ ታዳሽ ኃይልና ለዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ስትራቴጂካዊ አጋር እየሆነች መምጣቷን ተናግረዋል።
የባሕረ ሰላጤው ሀገራትም የሉዓላዊ ሀብት ፈንዶችን በመጠቀም በመሠረተ ልማት፣ በታዳሽ ኃይል፣ በቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስና በግብርና ዘርፎች ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እያደረጉ እንደሚገኙ አንስተዋል።
በቀጣይ ትብብርን በማጠናከር አስተማማኝና ሳቢ የኢንቨስትመንት ሕግና ፖሊሲ ማዕቀፍ በመፍጠር ፈጠራ የታከለበት ጠንካራ የትግበራና የክትትል ስልት ማቋቋም እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረትና የዲፕሎማሲ ማዕከል በመሆኗ የአህጉሪቷንና የባሕረ ሰላጤው ሀገራትን ስትራቴጂክ አጋርነት በማጠናከር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስርን ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።