የሀገር ውስጥ ዜና

ህገ ወጡ ሕወሓት የትግራይን ወጣቶች እያፈሰ ወደ ስልጠና ካምፕ እያስገባ ነው

By Mikias Ayele

July 22, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ህገ ወጡ ሕወሓት የክልሉን ወጣቶች እያፈሰ ወደ ስልጠና ካምፕ እያስገባ ነው አሉ፡፡

ህገ ወጡ ሕወሓት፣ የመደመር መንግሥት በተደጋጋሚ የሚያቀርብለትን የሰላም ጥሪ ችላ በማለት የጦርነት ጉሰማውን የቀጠለ ሲሆን፤ ቡድኑ በፕሪቶሪያ ስምምነት የተገኘውን የሰላም አማራጭ በመተው፣ የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር አፍርሶ የጦርነት ያለህ እያለ ይገኛል፡፡

ከመላው የክልሉ አካባቢዎች ወጣቶችን እያፈሰ በክልሉ ወደሚገኙ እና ወደ ኤርትራ የወታደራዊ የማሰልጠኛ ካምፖች እያጓጉዘ እንደሚገኝ ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።

ቤተሰብ ቡድኑ ለሚያደርገው የጦርነት ዝግጅት፣ ልጆቹ ወደ ውትድርና የስልጠና ካምፖች እንዳይወሰዱበት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ያለ ሲሆን የተወሰዱበትን ለማስለቀቅ በሚደረግ ትንቅንቅ የተረሸኑት በርካቶች ናቸው ብለዋል፡፡

በምሥራቃዊ ዞን በፅራእ ወምበርታ ወረዳ ሓይቅ መስሓል ከተማ በሚገኘው የህገ ወጡ ሕወሓት የውትድርና ማሰልጠኛ በትግራይ ወጣቶች ላይ ግፍ እየተፈጸመ እንዳለ የአካባቢው ነዋሪዎች ለፋና ዲጂታል መረጃ አድርሰዋል፡፡

ከአብዛኛው የትግራይ አካባቢ በቡድን አፈሳ የተማረሩ ወጣቶች ወደ ሌሎች ክልሎች እና ወደ አዲስ አባባ ከተማ ለመሸሽ በሚያደርጉት ጉዞ ቡድኑ አግቶ እየያዘ ወደ ማጎሪያ እያስገባቸው መሆኑንም ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡

ወጣቶቹ ከማሰልጠኛዎች ጠፍተው እንዳያመልጡ በቡድኑ ታጣቂዎች በሁሉም አቅጣጫዎች ተከብበዋል፡፡

ለማምለጥ የሞከሩም በካምፑ ጠባቂዎች እንደተረሸኑ ከአካባቢው ህብረተሰብ የደረሰን ጥቆማ አመለክቷል።

በተመሳሳይ በምስራቃዊ ዞን ኣፅቢ ወምበርታ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች ማለትም በቃልአሚን፣ በእሶት እና ከዓፋር በሚያዋስኑ ጫካዎች እጅግ አሰቃቂ ግፍ የሚፈፀምባቸው በወጣቶች የተሞሉ የማሰልጠኛ ካምፖች አሉ፡፡

በኣፅቢ ወረዳ በቃልአሚን ቀበሌ ልዩ ስሙ ውርጊሒት በሚባል ቦታ ሐምሌ 14 ቀን 2018 ዓ.ም የወረዳው አመራሮችና አርሚ 92 በመባል የሚታወቁ በአካባቢው የሰፈረው የቡድኑ ታጣቂ ሀይል ነዋሪውን በግድ ሰብስበው ‘ትግራይ ለታገሉት ብቻ ናት፣ ከእያንዳንዱ ቤት ቢያንስ አንድ ልጅ ትገብራላችሁ’ በማለት ህዝቡን ሲያስፈራሩና ሲያስለቅሱ መዋላቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ይጠቁማል።

በዚህ የተነሳ ሕብረተሰቡ ቡድኑ ‘ሌሊት መጥቶ ልጆቻችንን ይነጥቀናል’ በማለት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገብቷል።