የሀገር ውስጥ ዜና

መመካከር ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚጣል መሠረት ነው

መመካከር ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚጣል መሠረት ነው

By Melaku Gedif

July 22, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የሺህ ዓመታት የታሪክ ባለቤት፣ የበርካታ ቋንቋዎች፣ ባሕሎች፣ እምነቶችና ማንነቶች መኖሪያ ሀገር ናት።

ይህ ብዝኃነት የሀገሪቱ ሀብትና ጥንካሬ ቢሆንም፣ በአግባቡ ካልተያዘ የልዩነትና የአለመግባባት ምንጭ ሊሆን ይችላል።

ልዩነቶችን በግጭት ሳይሆን በውይይት ለመፍታት፣ የተለያዩ ዕይታዎችን በአክብሮት ለማዳመጥ እና የጋራ መፍትሔ ለመፍጠር የሚያስችለው መንገድ ሀገራዊ ምክክር ነው።

በመከናወን ላይ ያለው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ይህንን እሳቤ በተግባር እያሳየ ያለ አስፈላጊ መድረክ ነው።

ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተሳታፊዎች የሀገር ወሳኝ ጉዳዮችን በግልጽነትና በኃላፊነት በመወያየት፣ ልዩነቶቻቸውን በመደማመጥ እና የጋራ መፍትሔ ለማግኘት በቁርጠኝነት እየተሳተፉ ነው።

ይህም ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት የሚጥል ቁልፍ ጉዳይ ነው።

ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ማለት ዜጎቹ በሕግ ፊት እኩል የሚሆኑበት፣ ተቋማት በአግባቡ የሚሠሩበት፣ የፖለቲካ ልዩነቶች በውይይት የሚፈቱበት እና የሕዝብ መተማመን የተጠናከረበት ሀገር ማለት ነው።

ይህንን መሠረት ለመገንባት ደግሞ ሁሉን ያሳተፈ ምክክር ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

ዜጎች ሀሳባቸውን በነፃነት ሲገልጹ፣ ሌሎችንም በአክብሮት ሲያዳምጡ የጋራ እምነት ይጠናከራል። በዚህም የግጭት እድሎች እየቀነሱ የመግባባት ባሕል ይጎለብታል።

ሀገራዊ ምክክር የተለያዩ ሐሳቦችን አንድ ላይ በማምጣት የጋራ ራዕይን ለመገንባት የሚረዳ ሂደት ነው። በሀገር ደረጃ የሚነሱ ውስብስብ ጉዳዮች የሚፈቱት በአንድ ወገን አሸናፊነት ሳይሆን፣ በጋራ መግባባትና በሁሉም ወገኖች ተሳትፎ መሆኑን የዓለም ልምዶችም ያሳያሉ።

በመሆኑም የሀገራዊ ምክክር ሂደት የዛሬን ችግሮች ብቻ ሳይሆን የነገውን ትውልድ የሚጠቅም የመግባባት ባሕል ለመፍጠር ያግዛል።

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ላይ እየታየ ያለው የተሳታፊዎች የመደማመጥ ፍላጎት፣ የልዩነት ሀሳቦችን በአክብሮት የመቀበል አመለካከት እና የሀገርን ጥቅም ከሁሉ በላይ ለማስቀደም የታየው ቁርጠኝነት ለሂደቱ አበረታች ምልክት ነው።

እንዲህ ያሉ መድረኮች ዜጎች በጋራ የሚወስኑትን ውሳኔ እንዲያከብሩ ያግዛሉ። በተቋማት ላይ ያለውን መተማመንም ያጠናክራሉ።

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የጀመረው ሂደት ስኬታማ ሊሆን የሚችለው ሁሉም ዜጎች የራሳቸው ሚና እንዳላቸው ሲያምኑ እና በንቃት ሲሳተፉ ነው። መመካከር የአንድ ተቋም ወይም የአንድ ቡድን ተግባር ብቻ ሳይሆን የመላው ሕዝብ ኃላፊነት ነው።

የውይይት ባሕል በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤት፣ በማኅበረሰብ እና በሀገር ደረጃ ሲጠናከር ብቻ ዘላቂ ሰላምና የተረጋጋ ሀገረ መንግሥት ሊገነባ ይችላል።

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው መመካከር ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት፣ ለዘላቂ ሰላም፣ ለፍትሕ እና ለአንድነት የማይተካ መሣሪያ መሆኑን በተግባር እያስሰከረ ቀጥሏል።

የኢትዮጵያ የወደፊት ጥንካሬ በልዩነቶችን በመቻቻል፣ በመደማመጥ እና በጋራ መፍትሔ በመፈለግ ላይ የሚመሠረት እንደሆነ ጉባኤው ግልጽ መልዕክት እያስተላለፈ ይገኛል።

ይህን ሂደት በትዕግሥት፣ በኃላፊነት እና በቀጣይነት ማስቀጠል የሁሉም ዜጎችና ተቋማት የጋራ ኃላፊነት ነው።

#የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን