የሀገር ውስጥ ዜና

ብልፅግና ፓርቲ የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል የጀመራቸው ተጨባጭ ለውጦች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – አቶ አደም ፋራህ

By Melaku Gedif

July 22, 2026

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልፅግና ፓርቲ በፓርቲና በመንግሥት የተቀናጀ አመራር የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻል የጀመራቸው ተጨባጭ ለውጦች ተጠናክረው ይቀጥላሉ አሉ የብልፅግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ።

በ2018 በጀት ዓመት በፓርቲና በመንግሥት ቅንጅት በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በገበያ ማረጋጋትና በኑሮ ውድነት ቅነሳ ዙሪያ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን የገመገመው መድረክ ተጠናቅቋል፡፡

አቶ አደም በዚህ ወቅት÷ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የገበያ መረጋጋትና የኑሮ ውድነት ቅነሳ የመንግሥት መደበኛ ፕሮግራሞች ብቻ ሳይሆኑ የፓርቲው ዋና ዋና የፖለቲካ ተልዕኮዎች በመሆናቸው በሁሉም የአመራር እርከኖች በንቅናቄ ተመርተዋል ብለዋል።

ይህም ከዕቅድ አፈጻጸም ባለፈ በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን ነው ያመላከቱት፡፡

በሁሉም ክልሎች በሥራ ዕድል ፈጠራና በኑሮ ውድነት ቅነሳ ዘርፎች የሚታዩ መሻሻሎች መመዝገባቸውን ጠቁመው ÷ ያለውን የሀገሪቱን አቅምና የሕዝቡን ፍላጎት ከግምት በማስገባት ግን ከዚህ በላይ ሊሠራ የሚገባ ብዙ ሥራ እንዳለ አስገንዝበዋል።

“ሁለቱንም የትኩረት መስኮች በሕዝብ ንቅናቄ በመምራታችን ጉዳዩን እስከ ቀበሌ ድረስ የአመራር አጀንዳ ማድረግ ችለናል ፤ ይህም ተጨባጭ ለውጥ አስገኝቷል፤ አሁን ያለውን ጅምር ማጠናከርና ወደ ከፍተኛ ውጤት ማሸጋገር ይጠበቃል” ብለዋል።

አቶ አደም የፓርቲ አደረጃጀቶች እና አባላት በዘርፉ ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት በተጠናከረ መልኩ መቀጠል እንዳለበትና የእያንዳንዱን አካባቢ የልማት አቅምና የገበያ እውነታ መሠረት በማድረግ ለሕዝቡ ቀጥተኛ ጥቅም የሚያስገኙ ምርቶችን በመለየት የኑሮ ሁኔታን ማሻሻል የቀጣይ ትኩረት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

እንዲሁም የሕዝብ ባለቤትነትንና የተደራጀ ተሳትፎን በማጠናከር፣ ከአሰራር፣ ከአመለካከትና ከአስተሳሰብ ጋር የተያያዙ ማነቆዎችን በመፍታት ሥራዎቹን ዘላቂ፣ ተቋማዊና ሥርዓታዊ በሆነ አግባብ ማስቀጠል እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የ2019 በጀት ዓመት ዕቅዶች በተሻለ አፈጻጸም እንዲተገበሩ ሁሉም የፓርቲ መዋቅሮችና የመንግሥት ተቋማት በቅንጅት፣ በተጠያቂነትና በውጤት ተኮር አሰራር ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ጠይቀዋል።